ቀጥታ፡

በአማራ ክልል በድህረ ምርት የሰብል ስብሰባ ወቅት ብክነትን ለመቀነስ በዘመናዊ መሳሪያ የታገዘ ጥረት እየተደረገ ነው

ባህር ዳር፤  ታህሳስ 20 /2016 (ኢዜአ) ፡- በአማራ ክልል በድህረ ምርት የሰብል ስብሰባ ወቅት ሊደርስ የሚችለውን የምርት ብክነት  ለመቀነስ በዘመናዊ መሳሪያ የታገዘ ጥረት እየተደረገ  መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

ከአጨዳ ጀምሮ ምርቱ ተወቅቶ ወደ ጎተራ እስኪገባ 30 በመቶ ድረስ ምርት እንደሚባክን ቀደም ሲል የተደረጉ ጥናቶች ይጠቁማሉ።

በግብርና ቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ አግደው ሞላ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በ2015/2016 የምርት ዘመን በክልሉ በተለያየ የሰብል ዓይነት ከለማው 5 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት እስካሁን በ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር የደረሰ ሰብል ተሰብስቧል።


 

ቀሪውን ሰብል በቴክኖሎጂ በታገዘ አግባብ የመሰብሰብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ እስከ ጥር ወር መግቢያ ሙሉ በሙሉ ሰብስቦ ለማጠናቀቅ ስራው መቀጠሉን ተናግረዋል።

የምርት ብክነትን ለመቀነስም በ48 ኮምባይነሮችና በ272 አነስተኛ ዘመናዊ የሰብል መውቂያ መሳሪያዎች በመታገዝ በ344 ሺህ ሄክታር ላይ የለማ ሰብል መሰብሰብ መቻሉን ጠቅሰዋል።

አርሶ አደሩ በአጨዳ፣ በክመራና በውቂያ ሂደት ሊደርስ የሚችለውን የምርት ብክነት ከ30 በመቶ ወደ 26 በመቶ ዝቅ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

ምርቱ ወደ ጎተራ ከገባ በኋላም በነቀዝ፣ በአይጥና ሌሎች ተባዮች እንዳይበላ አንድ ሺህ 300 የብረት ጎተራና አንድ ነጥብ 5 ሚሊዮን አየር የማያስገባ የሰብል ማከማቻ ጆንያ ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ ይገኛል ብለዋል።

ባለፉት ዓመታትም 5 ሺህ 440 የብረት ጎተራዎችና ከአራት ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ ተባይን መከላከል የሚችሉ የእህል መያዣ ጆንያዎች ለአርሶ አደሩ ተሰራጭተው ጥቅም ላይ እንደዋሉም ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።

በምስራቅ ጎጃም ዞን የደብረ ኤልያስ ወረዳ አርሶ አደር ከፌ ይታው በሰጡት አስተያየት፤ በመኽሩ

ወቅት ባላቸው መሬት ያለሙትን የስንዴና የበቆሎ ሰብል ምርት ብክነትን ሊቀንስ በሚችል አግባብ እየሰበሰቡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

እስካሁን ከ2 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የደረሰ የሰብል ምርት መሰብሰባቸውን ጠቅሰው፤ ዘንድሮ ኮምባይነር ባለመቅረቡ መጠቀም እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

ያለሙትን የበቆሎ፣ ገብስ፣ ጤፍና ዳጉሳ ሰብል በየዓመቱ የሚሰበስቡት በሰው ጉልበት እንደሆነ የገለጹት ደግሞ በምዕራብ ጎጃም ዞን የሰከላ ወረዳ አርሶ አደር ሞገስ አይናለም ናቸው።

ከአጨዳ ጀምሮ እስከ ውቂያ ባለው የሰብል አሰባሰብ ሂደት ምርቱ ሳይባክን ለመሰብሰብ ጥረት እያደረጉ እንደሆነም አመልክተዋል።

ቀደም ሲል ምርቱ ወደቤት ከገባ በኋላ በነቀዝና ሌሎች ተባዮች እንዳይበላ በተሻሻለ ጆንያ በማስቀመጥ ጥራት ያለው ምርት ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንደሆኑም አውስተዋል።

በ2015/2016 የምርት ዘመን በአማራ ክልል በተለያየ የሰብል ዓይነት ከለማው መሬት 160 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ከግብርና ቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም