የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጆኦስፓሻል ኢኒስቲትዩት በዘርፉ ብቁ የሰው ሀይል እንዲኖር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጆኦስፓሻል ኢኒስቲትዩት በዘርፉ ብቁ የሰው ሀይል እንዲኖር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ ነው
ሐረር፤ ታህሳስ 20/2016(ኢዜአ):- የኢትዮጵያን ስፔስ ሳይንስና ጆኦስፓሻል ኢኒስቲትዩት በዘርፉ ብቁና የሰለጠነ የሰው ሀይል ለማፍራት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገለጸ።
የኢትዮጵያን ስፔስ ሳይንስና ጆኦስፓሻል ኢኒስቲትዩት 'ብሄራዊ የስፔስ እና አለም አቀፍ የጂ.አይ.ኤስ' ቀን ምክንያት በማድረግ በሐረር ከተማ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ አከናውኗል።
በግንዛቤ ማስጨበጫው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያን ስፔስ ሳይንስና ጆኦስፓሻል ኢኒስቲዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ እንደገለጹት፤ ኢንስቲዩቱ ከአጋር አካላት ጋር ሳተላይት አልምቶ የማምጠቅና የተገኘውንም መረጃ የመቀበል፣ የመተንተንና የመተግበር ስራዎችን እያከናወነ ነው።
የዘርፉ ቴክኖሎጂን የመማር፣ የማወቅና የመረዳት እንዲሁም ተመሳሳይ ቴክኖሎጂን የመስራት ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ከሰው ሃብት ልማት ጋር በተያያዘም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር በዘርፉ የሚታየውን የሰው ሃይል እጥረት ለመቅረፍ የስልጠናና ቴክኒክ ድጋፍ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም ተናግረዋል።
በ'ጂኦስፓሻል' ከከተማ ልማት ጋር በተያያዘ በመሬት አስተዳደር፣ በከተማ ፕላኒንግ፣ በቱሪዝምና በሌሎች ዘርፎች ለሚሰሩ ተቋማት መረጃን ከማቅረብ ባለፈ የአቅም ግባታ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።
ለመሬት ዝግጅት፣ ለካዳስተርና ለመሰረተ ልማት ግንባታ ዝርዝር የዲዛይን ዝግጅት ግብዓት ሆነው የሚያገለግሉ መረጃዎችን የማቅረብ ስራ ኢንስቲትዩቱ እያከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ኢንስቲትዩቲ የሚያከናውነውን ስራ ህብረተሰቡ በአግባቡ ተረድቶ እንዲጠቀም በተለያዩ መንገዶች የማሳወቅ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የሀረሪ ክልል ጨምሮ በአምስት ክልሎች ቀኑን ምክንያት በማድረግ ኢኒስቲቲዩቱ ያከናወነውን ስራዎች የማስተዋወቅና ግንዛቤ የመስጠት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
መድረኩ ክልሎች ላይ ያሉ ሀብቶችን በመለየት ሀብቶቹን አልምተው ለመጠቀምና ክህሎት ለማስጨበጥ ከፍተኛ አስተዋጽዎ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።
የሐረሪ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ሃላፊ አቶ ጀማል ኢብራሂም በበኩላቸው ኤጀንሲው በክልሉ በቱሪዝምና ሐረር ከተማ ያላትን እሴትና ባህል የሚያስተዋወቅ የዲጂታል መረጃ ቴክኖሎጂን የማልማት ስራ ማከናወኑን ተናግረዋል።
መድረኩ በተለይ ክህሎቱ ያላቸው ወጣቶችና ተማሪዎች በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጡ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።
በግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያን ስፔስ ሳይንስና ጆኦስፓሻል ኢኒስቲዩት በተጨማሪ ከኢትዮዽያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣንና ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከፍተኛ ሃላፊዎች፣ ተማሪዎችና ወጣቶች ተገኝተዋል።