ቀጥታ፡

አገራዊ ምክክሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ እየሰሩ መሆኑን ተፎካካሪ ፓርቲዎች አስታወቁ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 20/2016(ኢዜአ):-አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የያዘው ግብ አንዲሳካ አባላቶቻቸው ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረጉ መሆኑን የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናግረዋል።   

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን እጅግ መሰረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሁሉንም ያካተተ ምክክር በማካሄድ  የተሻለ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል።

በአገራዊ ምክክሩ ከሚሳተፉት ወሳኝ አካላት መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚገኙበት ሲሆን በምክክሩ ዙሪያ ኢዜአ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ቆይታ አድርጓል። 

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የፓርቲ አመራሮች አገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ተናግረዋል።

አገራዊ ምክክሩ የያዘው ግብ ሰፊ በመሆኑ ሂደቱ እንዲሳካ በውይይቱ ከመሳተፍ ባለፈ አባላቶቻቸው ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን እያደረጉ መሆኑን አመራሮቹ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሔር አንድነት ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚአብሔር "በአገራዊ ምክክሩ ለመሳተፍ ሁለንተናዊ ዝግጅት እያደረግን" ነው ብለዋል።

የአገሪቱን መጻዒ ዕድል ለመወሰንና ቁርሾዎችን በመቅረፍ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ምክክሩ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን አመላክተዋል።

"ሁላችንም ያለችን አንድ አገር ስለሆነች አገራችንን በሰላምና ብልዕግና ለማቆየት እንዲሁም የህዝባችንን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ አበክረን መስራት አለብን" ብለዋል።

የፖለቲካ አለመግባባቶችን በሰለጠነ አስተሳሰብና በመመካከር ለመፍታት አገራዊ ምክክሩ ትልቅ አማራጭ ይዞ መምጣቱን የተናገሩት ደግሞ የገዳ ቢሊሱማ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ መሳይ አበበ ናቸው። 

ፓርቲያቸውም ሆነ አባላቶቻቸው በምክክር ሂደቱ ለመሳተፍ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ግለሰብ የሃሳብ የበላይነት ገዢ እንዲሆን ሁላችንም አበክረን መስራት አለብን ብለዋል።

የአርጎባ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አቶ መሐመድ ሙሳ በበኩላቸው ፓርቲያቸው በሚንቀሳቀስባቸው ክልሎች አባላቶቻቸው ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እየሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል።


 

ልዩነቶቻችንን በመነጋገር ለመፍታት አገራዊ ምክክሩ ጥሩ ዕድል ይዞልን የመጣ በመሆኑ ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉም ጠቁመዋል።

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታህሳስ 20 ቀን 2014 ባካሄደው ሁለተኛ ልዩ ስብሰባው፤ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ  በአብላጫ ድምፅ ማጽደቁ ይታወሳል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም