ቀጥታ፡

መንግሥት ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ነፍጥ ላነገቡ ኃይሎች የሰላም በር መክፈቱ በበርካታ አካባቢዎች ሰላም እንዲፈጠርና ሕዝቡ ወደ ልማት እንዲያዞር አድርጓል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 20/2016(ኢዜአ):- መንግሥት ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ በሁሉም ክልሎች ነፍጥ ላነገቡ ኃይሎች የሰላም በር መክፈቱ በበርካታ አካባቢዎች ሰላም እንዲፈጠርና ሕዝቡ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር ማድረጉን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ገለጹ።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ ያጋጠመውን ድርቅ በተመለከተ ከሰሞኑ የሰጠው መግለጫ ፈፅሞ የተሳሳተ መሆኑንም ገልፀዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

ከሰላምና ደኅንነት አኳያ በየጊዜው የሚነሱና ያልተረጋጋ ድባብ ለመፍጠር የሚደረጉ ሙከራዎች ለሀገረ- መንግሥት ግንባታ ሂደት ተግዳሮቶች ሆነው መቀጠላቸውን አንስተዋል።

መንግሥት ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽንና መሰል ተቋማትን አቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ገልፀው፤ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥም በሁሉም ክልሎች ነፍጥ ላነገቡ ኃይሎች የሰላም በር መከፈቱን ገልፀው፤ በዚህም በተለያዩ ክልሎች አንፃራዊ ሰላም መፈጠሩንና ሕዝቡም እፎይታ እያገኘ መሆኑን ተናግረዋል።

በአንፃሩ የሰላም አማራጭ ያልፈለጉ ኃይሎች አሁንም ኃብት መዝረፍና የፖለቲካ ፍላጎትን በኃይል ለማሳካት አውዳሚና በታኝ አካሄድ መከተላቸውን ገልጸው፤ ነገር ግን ከሕዝብ እየተነጠሉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኦሮሚያ ክልል ከሸኔ ጋር ሁለት ዙር በታንዛኒያ በተደረገ ውይይት በአብዛኛው ጉዳዮች የተሻለ መግባባት ቢደረስም ከቡድኑ የሽብር እሳቤ የተነሳ ድርድሩ እንዳልተሳካ ገልፀዋል።

በዚህም ለሕዝብ ሰላም ሲባል መንግሥትም የሕግ ማስከበር ሥራውን በመቀጠሉ የሽብር ቡድኑ ከባድ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውደመት እንደደረሰበት ተናግረዋል።

በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው የሕግ ማስከበር ሥራም ክልሉን ከመፍረስ ከመታደግ ባሻገር አዲሱ የመንግሥት አመራር መዋቅር እስከ ቀበሌ ድረስ ዘርግቶ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑንና በሁሉም የክልሉ ወረዳዎች ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልፀዋል።

በክልሉ በታወጀው የሰላም ጥሪ በሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች ወደ ተሃድሶ ማዕከላት መግባታቸውን ጠቅሰው፤ ከእነዚህም መካከል 2 ሺህ 500 የቡድን መሳሪያዎችን የታጠቁ አመራሮች ያሉበት መሆናቸውን አንስተዋል።

ከሰላም ጥሪው ቀደም ብሎ በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩ 4 ሺህ የሚሆኑ ግለሰቦች የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ ሕብረሰቡ እየተቀላቀሉ መሆኑን ገልፀዋል።

ሁከትና ብጥብጥ በመምራት የተጠረጠሩ 360 ግለሰቦች ጉዳያቸው በሕግ እንደሚታይ ገልፀው፤ 280 የሚሆኑት ደግሞ በደረቅ ወንጀል ስለተጠረጠሩ ወደየዞናቸው መላካቸውን ጠቅሰዋል።

በክልሉ በተፈጠረው አንፃራዊ ሰላም ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ለማካሄድ የሚያስችል ውጤት መገኘቱን ገልጸው፤ ይህን ለማፅናትም የህብረተሰቡ ትብብር እንዲጠናከር ጠይቀዋል።

በክልል አሁንም ከሰላም ይልቅ በሁከትና ብጥብጥ በዝርፊያና ግድያ ሽብር ለመፍጠር የሚሞክሩ ኃይሎች ላይ ሕግ የማስከበር ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ሕዝብ ጥያቄዎች ከሌሎች ክልል ጥያቄዎች የተለዩ እንዳልሆኑ ገልፀው፣ ጥያቄዎች በአብሮነት፤ በሕብረ- ብሔራዊነት እና በመደመር መርህ ብቻ የሚመለሱ እንደሆኑ አንስተዋል።

አሁናዊ ተግዳሮቶችን ለመሻገርና ሁለንተናዊ ሰላም፣ ልማትና ብልፅግና ለማረጋገጥ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ያስፈልጋል ብለዋል።

በዚህም ላለፉት ሁለት ወራት ለ54 ሺህ አመራሮች የአቅም ግንባታ ሥልጠና መሰጠቱን አስታውሰዋል።

አሁንም በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ የቀበሌ አመራሮች ስልጠናው መቀጠሉን ገልጸው፤ የጋራ ትርክት ለመፍጠርና የተሻለ ነገ ለመገንባት ያለመ መሆኑን አንስተዋል።

በሌላ በኩል ሀገራዊ ኢኮኖሚ በሁሉም መስክ እየተነቃቃ መሆኑን ገልፀዋል።

በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ የግብርና ምርትና ምርታማነት ትኩረት  መደረጉን ገልፀው፤ የወቅቱ የመኸር አዝመራ አብዛኛው መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።

የሌማት ቱርፋት፣ የከተማ ግብርናና መስኖ ልማት ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀው፤ ጤናማ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማረጋገጥ የበጋ መስኖ ልማት ስራዎችን በአይነትና በመጠን የመጨመር ሂደት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ሜጋ ፕሮጀክቶችም በፍጥነትና በጥራት እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሕዳሴ እና ኮይሻ ኃይል ማመንጫ ግድቦች፣ የገበታ ለሀገር፣ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ሌሎች የከተማ ልማትና የመንገድ መሠረተ-ልማት ፕሮጀክቶችን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ፕሮጀክቶች አገራዊ ኢኮኖሚ መነቃቃት እንዲፈጠር ከማድረግ ባሻገር የከተማና የአካባቢ ገፅታ በመቀየር ትልቅ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ገልፀዋል።

ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ ልማትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ሰብዓዊ ድጋፍን በተመለከተ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ድጋፍ አደጋዎች በአማራ፣ ትግራይ፣ አፋርና ሌሎች ክልሎች 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዜጎች የድርቅ አደጋ አንዲሁም 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች የጎርፍ አደጋ እንደደረሰባቸው አስታውሰዋል።

ከሐምሌ ወር ጀምሮ ከዓለም አቀፍ ረጂ ተቋማት ጋር በመተባበር 1 ሚሊየን 725 ሺህ ኩንታል ወይም በገንዘብ ሲገመት ከ15 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ የሚሆን ሰብዓዊ እርዳታ መቅረቡን ገልጸዋል።

መንግሥት ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ከሰሞኑ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የተሰጠው መግለጫ ፈፅሞ የተሳሳተ መሆኑንም ገልፀዋል።

መንግሥት ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ በሁሉም ክልሎች ነፍጥ ላነገቡ ኃይሎች የሰላም በር መከፈቱ በበርካታ አካባቢዎች ሰላም እንዲፈጠርና ሕዝቡ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር ማድረጉን ተናግረዋል።

ፖለቲካና ስብዓዊ ድጋፍን ማገናኘት ተገቢነት እንደሌለው አንስተዋል።

በትግራይ ክልል  በአራት ዞኖች ድርቅ የተከሰተ መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግሥት ድጋፍ እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በሕዝብ ሽፋን የሚደረግ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ተቀባይነት እንደሌለውም ተናግረዋል።

በየትኛውም ክልል ከሰላም መደፍረስ አኳያ በሰብዓዊ አቅርቦት ላይ መስተጓጎል ተፈጥሮ ካልሆነ በስተቀር በረሃብ ምክንያት የሞተ ሰው አለ የሚል ግምገማ እንደሌለም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም