ቀጥታ፡

በውጭ የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት የሚያደርጉት ጉዞ ስኬታማ እንዲሆን እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 20/2016(ኢዜአ):- በውጭ የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት የሚያደርጉት ጉዞ ስኬታማ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን በልዩ ልዩ የዓለም ክፍል የሚገኙ የኢፌዴሪ ሚሲዮኖች አስታወቁ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር ) በቀረበው ጥሪ መሰረት በውጭ የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት የሚያደርጉትን ጉዞ በተመለከተ ከኢፌዴሪ ሚሲዮኖች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርትኳን አያኖ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ሚሲዮኖች ከዚህ በፊት በተካሄዱ ሀገራዊ ጥሪዎች የማስተባበር ልምድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡትን ጥሪ ለማስተባበር የጀመሯቸውን ስራዎች አጠናክረው እንዲቀጥሉ አስረድተዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እንድሪስ (ዶ/ር ) በበኩላቸው ጥሪውን ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ በውጭ የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን የሚኖራቸው ቆይታ መልካም እንዲሆን የሚያስተባብሩ ኮሚቴዎች ተቋቁመው በመስራት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

አክለውም ሀገራት በተለያዩ ጊዜያት ልዩ ልዩ ዓላማዎችን የሰነቁ፣ በዘርፍና በዕድሜ እርከን የተከፋፈሉ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት ጥሪዎችን እንደሚያከናውኑ ጠቅሰዋል፡፡


 

ከማዕከል እስከ ሚሲዮን በሚደረገው የተደራጀ ንቅናቄም የጥሪውን ዓላማ ለማሳካት ይሰራል ማለታቸውን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡

የሚሲዮን መሪዎችም እንዳሉበት ሀገር ሁኔታ በውጭ የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው የሚያደርጉትን ጉዞ ለማስተባበርና ስኬታማ ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም