በምዕራብ ሸዋ ዞን ከ68 ሺህ በላይ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች ለአርሶ አደሮች ተሰራጭቷል - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ሸዋ ዞን ከ68 ሺህ በላይ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች ለአርሶ አደሮች ተሰራጭቷል
አምቦ፤ ታህሳስ 20/2016 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በበጀት ዓመቱ አምስት ወራት ከ68 ሺህ በላይ ዘመናዊ የንብ ቀፎ ለአርሶ አደሮች መሰጠቱን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
በጽህፈት ቤቱ የንብ ሃብትና ሀር ልማት ባለሙያ አቶ ብርሃኑ ለቺሳ እንደገለጹት ዞኑ ለንብ ማነብ ስራ ምቹ በመሆኑ ይህንኑ መሰረት ያደረገ ስራ ሲሰራ ቆይቷል።
በዚህም በዞኑ የማር ምርት ለማሳደግ በበጀት ዓመቱ አምስት ወራት ለ4 ሺህ አርሶ አደሮች 68 ሺህ 876 ዘመናዊ ቀፎዎች መሰራጨቱን ገልጸዋል።
ይህም አርሶ አደሮቹ ምርታቸውንና ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግላቸው ገልጸው በዞኑ ባለፉት ሁለት ወራት ከ3 ሚሊዮን ኪሎ ግራም የማር ምርት ተገኝቷል።
ባለሙያው እንዳሉት እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ 6 ሚሊዮን ኪሎ ግራም ማር ለማምረት የታቀደ ሲሆን፤ በዞኑ በንብ ማነብ ስራ የተሰማሩት 12 ሺህ 702 ያህል አርሶ አደሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።
በንብ ማነብ ስራ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች በበኩላቸው ከመደበኛው የግብርና ልማት በተጓዳኝ ንብ በማነብ ስራ ላይ በመሰማራት ተጨማሪ ገቢ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
በዞኑ የአምቦ ወረዳ አርሶ አደር ቦንሳ ፈይሳ በእርሻ ማሳቸው አካባቢ ባላቸው ዘመናዊ ቀፎዎች ዘንድሮ እስከ 60 ኪሎ ግራም ማር ማግኘት እንደቻሉ ገልጸዋል፡፡
ከማሩ ሽያጭ ጥሩ ገቢ በማግኘታቸው አሁን ያላቸውን ስድስት ባህላዊ የንብ ቀፎ ወደ ዘመናዊ ቀፎ ለመቀየር መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡
የንብ ማነብ ስራ እፅዋት በማልማት ከተሰራ በቂ ምርት በመስጠት ከእርሻ ስራቸው በተጓዳኝ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት እንደሚያስችላቸው በመረዳት ልማቱን አስፋፍተው መቀጠላቸውን ገልጸዋል፡፡
የቶኬ ኩታዬ ወረዳ አርሶ አደር ዴረሳ በንቲ በበኩላቸው በአስር ዘመናዊ ቀፎ ንብ በማነብ ከማርና ሰም ምርት ሽያጭ ከ150 ሺህ ብር በላይ ተጨማሪ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
በአካባቢያቸው እየተሰሩ ያሉ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራዎች ለውጤታማነታቸው አስተዋፅኦ በማበርከቱ አሁንም የችግኝ ተከላና የእፅዋት ማልማት ሥራን በማሳቸው እያስፋፉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የንብ ማነብ ስራን የሚያከናውኑት ከመደበኛ እርሻ ጐን ለጐን በመሆኑ ከዘርፉ ባገኙት ገቢ ኑሯቸውን እያሻሻሉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የደንዲ ወረዳ አርሶ አደር አበራ ፋና እንዳሉት ካላቸው አምስት ዘመናዊ የንብ ቀፎ በዓመት ሁለት ጊዜ ከሚቆርጡት ማር ከ300 ኪሎ ግራም በላይ ምርት እያገኙ ነው፡፡
ከምርቱ ሽያጭ በሚያገኙት ተጨማሪ ገቢ በመበረታታት ዘንድሮ 12 ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን በማከል ስራውን ማስፋፋታቸውን ተናግረዋል፡፡