ለምርት ዘመኑ ተገዝቶ የተጓጓዘው የአፈር ማዳበሪያ ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ደረሰ - ኢዜአ አማርኛ
ለምርት ዘመኑ ተገዝቶ የተጓጓዘው የአፈር ማዳበሪያ ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ደረሰ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 20/2016(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለ2016/17 የምርት ዘመን ከውጭ ከገዛው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ በዘጠኝ ዙሮች 4 ሚሊዮን 380 ሺህ ኩንታል ጂቡቲ ወደብ መድረሱን አስታውቋል።
ከውጭ ከተገዛው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ዛሬ 550 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ የጫነች መርከብ ጂቡቲ ወደብ መድረሷን ተከትሎ የተጓጓዘው የአፈር ማዳበሪያ መጠን ወደ 4 ሚሊዮን 380 ሺህ ኩንታል መድረሱ ተገልጿል።
ከዚህ ውስጥ ከ3 ሚሊዮን 618 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ከወደብ ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዞ በመሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበር አማካኝነት አርሶ አደሮች ጋር እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑም ተጠቅሷል።
በመጪው 20 ቀናት ውስጥም በሦስት መርከቦች ተጨማሪ 2 ሚሊዮን 90 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ጂቡቲ ወደብ እንደሚደርስ ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን መረጃ እንደሚያመለክተው በአጠቃላይ ወደ 15 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ የማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሟል።
ኮርፖሬሽኑ የኤን ፒ ኤስ አይነት ማዳበሪያ ግዥ ሙሉ በሙሉ የፈጸመ መሆኑንና ቀሪ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ዩሪያ ማዳበሪያ ግዥ ለመፈጸም እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑም ተጠቁሟል።