ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 20/2016 (ኢዜአ)፦ ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ሕብረተሰቡን በማንቃትና ብርቱ ተሳትፎ በማድረግ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ይገኛል።
ውይይቱ እየተካሄደ ያለው "ለሀገራዊ ምክክር እና ሀገራዊ መግባባት የኪነ-ጥበብ፣ የማስታወቂያ እና የሁነት ዝግጅት ተቋማትና ባለሙያዎች ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ ነው።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ ሀገራዊ ምክክሩ የታለመለት ዓላማ ከግብ እንዲደርስ የሁሉንም ዜጋ እና ተቋማት ርብርብ የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
በተለይም የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ዜጎች በአገራዊ ምክክሩ ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉና ባለሙያዎቹ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ሀገራዊ ምክክሩ ወሳኝ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ሚዲያን በመጠቀም ለሕዝብ ቅርብ የሆኑ ሥራዎችን በመሥራት ለስኬታማነቱ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱም አሳስበዋል።
የውይይት መድረኩ ስለ ሀገራዊ ምክክር ምንነትና አስፈላጊነት፣ ኮሚሽኑ እስካሁን ስላከናወናቸው አበይት ተግባራት ገለፃ እየተደረገ ይገኛል።
በተጨማሪም የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ለማስቻል ሰፊ ምክክር የሚደረግ ይሆናል ብለዋል።