ከ239 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ከተጠርጣሪ አዘዋዋሪ ግለሰቦቹ ጋር ተያዙ - ኢዜአ አማርኛ
ከ239 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ከተጠርጣሪ አዘዋዋሪ ግለሰቦቹ ጋር ተያዙ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 20/2016 (ኢዜአ)፦ በ1 ሳምንት ውስጥ ከ239 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ከ17 ተጠርጣሪ አዘዋዋሪዎች ጋር መያዙን የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።
የጉምሩክ ኮሚሽን ከታህሳስ 12 እስከ 18/2016 ዓ.ም ባደረገው ክትትል 131 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ገቢ እና 107 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ በድምሩ 239 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ይዟል።
በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሀኒት፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ የመኪና መለዋወጫ፣ የምግብ ዘይት እና የተለያዩ አገራት ገንዘቦች እንደሚገኙበት ተገልጿል።
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ የጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ የፌደራል እና የክልል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ የተያዙ መሆናቸውም ተጠቅሷል።
ኮንትሮባንዱን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 17 ተጠርጣሪዎችን እና ዘጠኝ ተሽከርካሪዎችንም በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።