የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሪፖርት በስደተኞች አያያዝ ላይ ያሉ ለውጦችን ያላካተተ በመሆኑ መታረም ይኖርበታል - የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሪፖርት በስደተኞች አያያዝ ላይ ያሉ ለውጦችን ያላካተተ በመሆኑ መታረም ይኖርበታል - የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 19/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሪፖርት በስደተኞች አያያዝ ላይ የተመዘገቡ የቅርብ ጊዜ ለውጦችን ያላካተተ በመሆኑ ሊታረም እንደሚገባው የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት አሳሰበ።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በተመለከተ ታህሳስ 15/2016 ዓ.ም ሪፖርት ማውጣቱ ይታወቃል።
የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት የኮሚሽኑን ሪፖርት አስመልክቶ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ ኮሚሽኑ በስደተኞች ጉዳይ ላይ በጎ ተጽእኖ ለማሳደር እያደረገ ላለው ጥረት እውቅና እንደሚሰጥ ገልጿል።
ይሁንና አገልግሎቱ በሪፖርቱ ይዘትና አቀራብ ላይ ቅሬታ እንዳለው አስታውቋል።
ሪፖርቱ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለስደተኞች የሚያደርገው ድጋፍ በተቀዛቀዘበት ኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ ኃላፊነት ለመወጣት እያደረገች ያለውን ጥረት ከግምት ውስጥ ማስገባት ነበረበት ብሏል።
የኮሚሽኑ ሪፖርት ከመውጣቱ አስቀድሞ ተቋሙ በግኝትነት ባቀረባቸው ጉዳዮች ላይ አስተያየት እንዲሰጡ አለመጠየቁም መታረም ያለበት ክፍተት እንደሆነና በቅርብ የተመዘገቡ ለውጦች ላይ ትኩረት አለማድረጉንም ነው አገልግሎቱ የገለጸው።
ከስደተኝነት ምዝገባ፣ሰነድ ማግኘትና የስደተኝነት ሁኔታ አወሳሰንን በተመለከተ፣ ቀድሞ የገቡ የሶሪያና የመን ጥገኝነት ጠያቂዎችን በልዩ ሁኔታ ውሳኔ ለመስጠት ጥናት ተደርጎ ምላሹ በሂደት ላይ ያለና ከጎረቤት ሀገራት ለሚገቡ ስደተኞችም ለድንበር ቅርብ በሆኑ ማዕከላት የጥገኝነት ጠያቂዎች ምዝገባ እየተከናወነ መሆኑን አብራርቷል።
በተለይም አዲስ አበባ የስደተኞች ምዝገባ እንደቆመ ተድርጎ በሪፖርቱ መገለጹ አጠቃላይ የጥገኝነት ጠያቂዎችን ቅበላ ሂደትና አሠራር ያላገናዘበ መሆኑንም እንዲሁ።
የጎረቤት አገራት ስደተኞች ምዝገባ በድንበር አካባቢ በመሆኑ በአዲስ አበባ ምዝገባ ተቋርጧል መባሉ ተገቢነት እንደሌለው፣ አዲስ የተወለዱ የስደተኛ ልጆችን በተመለከተም በተጠቀሰው ዓመት ብቻ 26 ሺህ 588 ስደተኞች መመዝገባቸውን ጠቅሷል።
በስደተኞች የመታወቂያ እድሳትና አዲስ መታወቂያ አሰጣጥን በተመለከተ፣ በጠቅላላ 14 ሺህ 821 ማስረጃዎች በስደተኝነት ለተመዘገቡ መሰጠቱና ስራው በዘመቻ መልክ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጿል።
ፍትህ የማግኘት መብትን በተመለከተ፣ፍትሕ የማግኘት መብታቸው እንዲከበር በስፋት እየተሰራና በተወሰኑ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች የተዘዋዋሪ ችሎት አገልግሎት እየተሠጠ መሆኑ እንዲሁም ከመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ለስድተኞች ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ ሪፖርቱ አለማካተቱን ጠቅሶ ቅሬታውን ጠቁሟል።
ማህበራዊና መሰረታዊ አገልግሎቶችን በተመለከተም በዓለም አቀፉ ኃላፊነትና ጫና መጋራት መርህ መሰረት ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚጠበቅ ድጋፍ ከደረጃ በታች መሆኑን የትምህርትና ጤና በጀት ቅናሽን ጠቅሶ አብራርቷል።
በቀጣይም ሰብዓዊ እርዳታ ውስንነቶች በቋሚነት እንዲፈቱ፣ የሶስተኛ አገር ዕድሎች እንዲስፋፉና ስደተኞች ክብራቸው ተጠብቆ በፈቃደኝነት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ከኮሚሽኑ ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ እንደሆነም ነው አገልግሎቱ የገለጸው።