ቀጥታ፡

የቡና ምርት ከአሰባሰብ እስከ ገበያ ያለውን የሂደት ጥራት ለማሳደግ የቡና አምራች አርሶ አደሮችን በዕውቀት የማጎልበት ስራ ትኩረት ተሰጥቶታል

ዲላ፤ታህሳስ 19/2016 (ኢዜአ)፡- የቡና አምራች አርሶ አደሮች ዘመናዊ አሰራር እንዲከተሉ ነባር እውቀታቸውን በማጎልበት የቡና ምርትና ጥራትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ገለጸ።

በቡና ልማት የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ዓላማ ያደረገ የአርሶ አደር የማሳ ላይ ትምህርት የውይይትና የስልጠና መድረክ በዲላ ከተማ ተካሄዷል።

በባለስልጣኑ የኢንዱስትሪ ግብዓት አቅርቦትና የጥራት ቁጥጥር ዘርፍ ሃላፊ አቶ አዲሱ መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት፤ የቡና ምርት ከአሰባሰብ እስከ ገበያ ያለውን የሂደት ጥራት ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።

የህግ ማዕቀፍ ከመዘርጋት ጀምሮ የአርሶ አደሩን አቅም እስከ መገንባት የደረሱ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

በተለይ የቡና ምርትን በጥራት ላዘጋጀ አርሶ አደር የተሻለ ዋጋ የሚያገኝበትን የአሰራር ስርዓት መዘርጋት መቻሉን ለአብነት አንስተዋል።

እንዲሁም አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ በማድረግና በአርሶ አደር የማሳ ላይ ትምህርት አርሶ አደሩ እርስ በእርሱ እንዲማማር ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ምርትና ጥራትን ለማሻሻል ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ከፍተኛ የሆነ የቡና ምርት ቢኖርም ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርበው ግን እጅግ ዝቅተኛ ነው የሚሉት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡናና ቅመማ ቅመም ባለሰልጣን የምርት ዝግጅትና ገበያ ልማት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ኪዳኔ ገረሙ ናቸው።


 

ባለፈው ዓመት ከ216 ሺህ ቶን በላይ ቡና ማምረት ቢቻልም ለውጭ ገበያ የቀረበው 20 በመቶ የሚሆነው ብቻ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ለዚህም ህገወጥ ንግድና የሀገር ውስጥ የቡና ፍጆታ ከፍተኛ መሆን ጫና ቢያሳደርም በአዘገጃጀት ወቅት የሚከሰት የቡና ጥራት መጓደል የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል ብለዋል።

ችግሩን በመቅረፍ ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርበውን የቡና መጠን ለማሳደግ ከምርት አሰባሰብ እስከ ግብይት የተሻሻሉ አሰራሮችን እንዲጠቀም የአርሶ አደሩን እውቀት የማጎልበት ስራ በቅንጅት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ የአርባ ምንጭ እጽዋት ጥበቃ ክሊኒክ ማዕከል ዳይሬክተር ሙላለም መርሻ በበኩላቸው ቡና ትልቁን ድርሻ የሚሸፍን የሃገራችን የወጪ ንግድ ምርት ነው። 

ይሁንና በአመራረትና በዝግጅት ወቅት በሚከሰት የጥራት ችግር የዘርፉ ተጠቃሚነት በተለያዩ ተግዳሮቶች እንዲታነቅ ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

ለዚህም ግንባር ቀደም ተጎጂ የሆነው አርሶ አደሩ መሆኑን ጠቅሰው የአርሶ አደርን ግንዛቤ የማዳበሩ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግርዋል።

በወረዳው ከ12 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና የተሸፈነ ቢሆንም የቡና እርጅና የምርታማነትና ጥራት ፈተና መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ በጌዴኦ ዞን ኮቾሬ ወረዳ የቡና ባለሙያ አቶ ፀጋዬ ተካ ናቸው።


 

ችግሩን ለማቃለልም በጉንደላና በነቀላ የቡና እድሳት ስራዎች የአርሶ አደር የማሳ ላይ ትምህርት ስርዓትን በመዘርጋት እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በመድረኩ ላይም የቡና ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች፣ የምርምር ተቋማት ተወካዮች፣ አርሶ አደሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም