ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገራዊ ጥሪውን ተከትሎ ወደ አገር ቤት ለሚገቡ ለሁለተኛው ትውልድ የዳያስፖራ አባላት የአየር ቲኬትና የሆቴል መስተንግዶ ዋጋ ቅናሽ አደረገ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 19/2016(ኢዜአ)፦  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ አባላት ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ ወደ አገር ቤት ለሚገቡ የዳያስፖራ አባላት የአውሮፕላን ትኬትና የሆቴል መስተንግዶ ዋጋ ቅናሽ ማድረጉን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ገለጸ።  

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በውጭ አገራት ለሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ የዳያስፖራ አባላት በሦስት ዙር ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ባሳለፍነው ሳምንት ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ በቱሪዝም ሚኒስቴር የሚመራና የተለያዩ የፌዴራልና የክልል ተቋማት የተሳተፉበት  ዐብይ ኮሚቴ ተቋቁሞ የሁለተኛ ትውልድ የዳያስፖራ አባላቱን ለመቀበል ዝግጅት ማጠናቀቁ ይታወቃል።  

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ሥራ ዘርፍ ዋና ኃላፊ ለማ ያዴቻ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተለያዩ ጊዜያት ለዳያስፖራ አባላት ጥሪ ሲያቀርቡ አየር መንገዱም የበኩሉን ኃላፊነት ሲወጣ ቆይቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሁለተኛው ትውልድ የዳያስፖራ አባላት ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ ወደ አገር ቤት  ለሚገቡት የዳያስፖራ አባላት  አየር መንገዱ  ከ15 እስከ 20 በመቶ የአውሮፕላን ቲኬት ቅናሽ ማድረጉን ገልጸዋል።

እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አካል በሆነው የስካይ ላይት ሆቴል ለሚያርፉ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም በተመሳሳይ ከ15 እስከ 20 በመቶ ቅናሽና ለእንግዶቹም ልዩ ዝግጀት ማደረጉን ዋና ኃላፊው አብራርተዋል።

ሁለተኛ ትውልድ የዳያስፖራ አባላት ከታህሳስ 20 ቀን 2016 እስከ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም ነው  በሦስት ዙር ወደ አገራቸው እንዲመጡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ያቀረቡት።  

የመጀመሪያ ዙር ከታህሳስ 20 እስከ ጥር 20/2016 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን 'connect to your multi culture' በሚል መሪ ኃሳብ እንደሚከናወን ተጠቅሷል። 

ሁለተኛው ዙር ደግሞ 'connect to your history' በሚል መሪ ኃሳብ ከየካቲት ወር 2016 ጀምሮ እስከ ክረምት መባቻ የሚዘልቅ መሆኑም እንዲሁ። 

ሦስተኛው ዙር 'live your legacy' በሚል ከ2016 ዓ.ም የክረምት መግቢያ ጀምሮ እስከ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተገልጿል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም