ሰመራ ዩኒቨርሲቲ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በመሬትና መሬትነክ ምርምር የልህቀት ማዕከል ለመሆን ከ2017 ጀምሮ ወደ ትግበራ ምዕራፍ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 19/2016(ኢዜአ)፦ሰመራ ዩኒቨርሲቲ በቆላማና ርጥበት አጠር አካባቢ ግብርና፣ በቱሪዝም፣ በመሬትና መሬትነክ የምርምር መስኮች የልህቀት ማዕከል መሆን የሚያስችለውን የትግበራ ምዕራፍ በ2017 ዓ.ም እንደሚጀምር ገለጸ።

የዩኒቨርቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር መሀመድ ዑስማን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲዎች በተልዕኮና የትኩረት መስክ መደልደላቸውን ተከትሎ ሰመራ ዩኒቨርሲቲም በተግባር ሳይንስ የልህቀት ማዕከል  እንዲሆኑ ከተመደቡ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ሆኗል።

ዩኒቨርሲቲው ትኩረት እንዲያደርግባቸው የተለዩ የተልዕኮ የምርምር ዘርፎችም፣ የቆላማና ርጥበት አጠር አካባቢ ግብርና፣ ቱሪዝም፣ ማዕድንን ጨምሮ የመሬትና መሬትነክ ምርምር ናቸው ብለዋል።

ይህን መነሻ በማድረግም ከአጠቃላይ የትምህርት ተቋምነት ወደ ተግባር ሳይንስ የልህቀት ማዕከል መሸጋገር የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የስርዓተ ትምህርት ክለሳ፣  የትኩረት መስክን መሰረት ያደረገ የሰው ሀብት አደረጃጀት፣ ለተልዕኮው መሳካት የሚያግዙ የምርምር መሰረተ ልማቶችን  እያሟላ መሆኑን ተናግረዋል።

አርብቶ አደሩን ጨምሮ በአፋር ክልልና በአካባቢው ከሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ጋር በመተሳሰር የተግባር ትምህርት መስጠት የሚያስችል ዝግጅት እየደረገ ነው ብለዋል።

የቅድም ዝግጅት ምዕራፉን በማጠናቀቅ ወደ ትግበራ ምዕራፍ ለመግባት መሰረት የሚሆኑ ዝግጅቶችም 60 በመቶ መድረሳቸውን ጠቅሰዋል።

በቱሪዝም፣ በግብርና እና በመሬትና መሬት ነክ(የስነ ምድር፣ የማዕድንና ሌሎችም) የምርምር ዘርፎች የልህቀት ማዕከል መሆን የሚያሰችለውን የትግበራ ምዕራፍም በ2017 ዓ.ም እንደሚጀምር ተናግረዋል።

የሰመራ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢው ላለው ማህበረሰብ የኢኮኖሚ መሻሻል ሚናውን እንደሚያጠናክር ገልጸው በአቅም ግንባታ ዘርፍ ሰፋፊ ስራዎች እያከናወነ ነው ብለዋል።

የአፋር ስርዓተ ምህዳርን ታሳቢ ያደረጉ የአትክልትና ፍራፍሬ የምርት ማሻሻያ ምርምሮችን እያካሄደ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የዩኒቨርቲው የእንስሳት ህክምና ተማሪዎች የእንስሳት ጤና ማሻሻል ላይ ምርምሮችንና የክትባት አገልግሎት እንደሚሰጡ ጠቁመው፤ ይህም ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ሊያሳካው ላሰበው የልህቀት ማዕከልነት መንገድ ጠራጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

 አፋር በርካታ የመስህብ ስፍራዎች ያሉት መሆኑን የገለጹት ዶክተር መሀመድ፤ በተለይም የሉሲ፣ የኤርታሌ፣ ዳሎልና ሌሎችም ውብ ተፈጥሮ መገኛነቱን አንስተዋል።

ከዚህም ባለፈ አካባቢው በምሽት የጠራ ሰማይና ከዋክብት የሚታዩበት በመሆኑ ለአስትሮ ቱሪዝም ትልቅ ሚና እንዲኖረው እንሰራለን  ብለዋል።

 በቀይ ባህር አቅጣጫ የሚመጡ ጎብኝዎች አፋርንና የተቀረውን የኢትዮጵያ ክፍል እንዲጎበኙ ለማድረግና ቀጣናዊ የባህል ትስስርን ለማጠናከር ማቀዳቸውንም ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም