በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል የማህበረሰብ አቀፍ ዘመቻ ተግባራዊ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል የማህበረሰብ አቀፍ ዘመቻ ተግባራዊ እየተደረገ ነው
ሚዛን አማን ፤ ታህሳስ 19/2016 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የወባ ወረርሽኝን ስርጭት ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመከላከል እንዲቻል የማኅበረሰብ አቀፍ ዘመቻ ላይ ትኩረት በማድረግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ ።
የቢሮው ምክትልና የፕሮግራሞች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኃይሌ ዘውዴ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የወባ ወረርሽኝን ስርጭት ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመከላከል እንዲቻል ማኅበረሰቡን ያሳተፈ ሥራ መስራት ላይ ትኩረት በማድረግ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።
የወባ በሽታ ስርጭት በክልሉ ውስጥ ስጋት እየሆነ በመምጣቱ እያንዳንዱ ማኅበረሰብ የሚጠበቅበትን የመከላከል ኃላፊነት እንዲወጣም ይህ ዘዴ ተመራጭ መሆኑን ተናግረዋል።
የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል በርካታ ሥራዎች እንደ ቢሮ ቢሰሩም ታች ላይ የአፈጻጸም ክፍተት በመኖሩ በሚፈለገው ልክ በሽታውን ለመከላከል አልተቻለም ብለዋል።
የተሰራጨውን አጎበር ለሌላ ጥቅም ማዋል፣ መድኃኒትን በአግባቡ ተጠቅሞ ያለመጨረስና የአካባቢ ንጽህና አጠባበቅ ሥርዓትን ቀጣይነት ያለው አለማድረግ የመከላከል ተግባሩ ላይ የሚታዩ ዋና ዋና ክፍተቶች መሆናቸውን አመላክተዋል።
በ2015 ዓ/ም አማካይ የወባ ስርጭት መጠን 67 በመቶ እንደነበር ገልጸው በዘንድሮ ዓመት ካለፉት 5 ወራት ወዲህ ብቻ ያለው የወባ ስርጭት 57 በመቶ መድረሱን ጠቁመዋል።
ለዚህም የወባ ስርጭትን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመግታት ማኅበረሰብ ተኮር የመከላከል ሥራን በልዩ ትኩረት ለመተግበር ወደ እንቅስቃሴ መገባቱን አክለዋል።
እስከታችኛው መዋቅር ቀበሌና መንደር ድረስ "ወባን መከላከል ከእኔ ይጀመራል" በሚል መሪ ቃል ከኅብረተሰቡ ጋር ውይይት በማካሄድ ለመከላከል ሥራው ውጤታማነት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
የበሽታው ስርጭት እስካሁን በመጣንበት የመከላከል ዘዴ ብቻ የሚገታ ባለመሆኑ በዘመቻ መልክ በጋራ ለመከላከል ከጤና ተቋማት ውጭ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ተቋማት የተካተቱበት ግብረ ሃይል መዋቀሩን ጠቁመዋል።
ማኅበረሰቡ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን የማፋሰስና የአካባቢውን ንጽህና የመጠበቅ ሥራን ዘወትር እየተገበረ ባህል እንዲያደርግ ግብረ ኃይሉ በአጽንኦት እንደሚከላከል አመላክተዋል።
እንደ ክልል የተሰራጨው ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ አጎበር የደረሰበትና የጤና ተቋማት የሕክምና ሂደት እንዲሁም ለዞኖች የተሰራጨው 2 ሺህ 185 ኪሎ ግራም የወባ ትንኝ መግደያ ኬሚካል የርጭት ሂደት በወባ መከላከል ንቅናቄ ይፈተሻል ነው ያሉት።
በክልሉ የወባ ስርጭት ጫና ከሚታይባቸው ዞኖች አንዱ የምዕራብ ኦሞ ዞን ሲሆን በአሁን ወቅት የስርጭት ምጣኔው 65 በመቶ መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሺማጂ ጉርጭማ ተናግረዋል።
በሽታውን ለመከላከል ከ135 ሺህ በላይ የአልጋ አጎበር የተሰራጨ ቢሆንም አብዛኞቹ ለሌላ አገልግሎት እየዋሉ በመሆኑ በሽታውን በአግባቡ ለመከላከል አልተቻለም ብለዋል።
የመከላከያ ዘዴን በአግባቡ ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ የግንዛቤ ትምህርት በዘመቻ ለኅብረተሰቡ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ ማጂ ወረዳ የኬልት ቀበሌ ነዋሪ ሻምበል ባሻ ማሙዴ እንዳሉት፤ የወባ በሽታ ከህጻን እስከ አዋቂ በከፍተኛ ሁኔታ እያጠቃ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያስከተለ ነው።
''በመሆኑም በተሰጠን ትምህርት መሰረት ከደጃችን ጀምሮ በየመንደሩ ከሌሎች ነዋሪዎች ጋር በመሆን የመኖሪያ አካባቢያችንን የማጽዳትና ያቆሩ ውሃዎችን የማፋሰስ ሥራን እየሰራን ነው'' ብለዋል ።
ሌላዋ የማጂ ወረዳ 01 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሲቲና አህመድ አካባቢው ደጋ በመሆኑ ከዚህ ቀደም ወባ እንደማይከሰት ገልጸው አሁን ላይ ስርጭቱ ከፍ እያለ በመምጣቱ አጎበር እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል።
በመንግስት የሚሰራጩ የመከላከያ ግብዓቶች በአግባቡ ከመጠቀም ባሻገር እንደ ማኅበረሰብ የሚጠበቅብንን ሀላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ነን ብለዋል።