ቀጥታ፡

በአካባቢያችን የሰፈነው ሰላም የልማት ሥራ ላይ እንድናተኩር አድርጎናል- የምዕራብ ኦሞ ዞን ነዋሪዎች

ሚዛን አማን፤ ታኅሣሥ 19/2016(ኢዜአ)  የክልሉ መንግስት በተቀናጀ መንገድ የአካባቢያችንን ሰላም ለማረጋገጥ ባከናወናቸው ውጤታማ ሥራዎች በተለያዩ የልማት ተግባራት ላይ  እንድንሰማራ  አድርጎናል ሲሉ የምዕራብ ኦሞ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።

ነዋሪዎቹ በአካባቢያቸው የሰፈነው ሰላም በልማት ተደግፎ ዘላቂ እንዲሆን ተግተው እንደሚሰሩም ተናግረዋል። 

የማጂ ወረዳ ነዋሪ አቶ ወርቁ ሲሪ ለኢዜአ እንዳሉት፤ አካባቢው ከልማት ይልቅ የግጭት እና የዝርፊያ ወንጀል ጉዳይ ብቻ የሚነሳበት ነበር።

ይሁን እንጂ የክልሉ መንግስት ባደረገው የውይይት እና የእርቀ ሰላም መድረክ ምክንያት ከዚህ ቀደም የነበሩ የእርስ በእርስ ግጭቶች በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሳቸውን ገልጸዋል።

''ሰላምን የማምጣት ኃላፊነት በእጃችን በመሆኑ ወደ ቀልባችን ተመልሰን በመነጋገርና ያሉንን የሰላም ማጠናከሪያ ዕሴቶቻችንን በመጠቀም የግጭት ምክንያቶቻችን እየፈታን ወደ ልማት ሥራ እየተሸጋገርን ነው'' ብለዋል።

ከአሁን በኋላ ወጣቱ ወደ ግጭትና ዝርፊያ እንዳይገባ የእርሻ ሥራን ማላመድና ሌሎች የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ላይ ተግባር ትኩረት በመደረጉ መጪው ጊዜ  የተሻለ እንደሚሆን ዕምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

የሱሪ ወረዳ ነዋሪ አቶ ባርባኩ ኤሌኪዩብ በበኩላቸው በአካባቢያቸው ላይ ሰላም ሰፍኖ የተፈጠረውን መረጋጋት በመጠቀም በእርሻ ልማት ስራ ላይ በስፋት እንደተሰማሩ ገልጸዋል።

''ሰላሙን ለማጽናት ደግሞ ሰርቶ ከራስ አልፎ ለሌላው ተርፎ ውጤቱን ማሳየት ይገባናል'' ያሉት አስተያየት ሰጪው በግጭትና በህገወጥ ተግባር ያጠፋነውን ጊዜ አሁን በልማት ውጤት ለመካስ ተነስተናል ብለዋል።

መልማት የሚችል ሰፋፊ የእርሻ መሬት ያለበት አካባቢ ቢሆንም አርብቶ አደር እንደመሆናችን እህል ዘርተን ለመብላት የተሞክሮ ችግር አለብን ያሉት አቶ ባርባኩ አሁን ላይ የተጀመሩ ጥረቶች እንዲስፋፉ መንግስት ሊደግፍ እንደሚገባ አንስተዋል።

የምዕራብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ኬኒ በዞኑ እየታየ ያለውን የሰላም ለውጥ ይበልጥ ለማጠናከር የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በአካባቢው ለመዘርጋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በዞኑ የሱሪ እና ማጂ ወረዳ አዋሳኝ ላይ የሰብል ምርጥ ዘር ማምረቻ እርሻ እንዲጀምር 5 ሺህ ሄክታር መሬት ማስረከባቸውን ተናግረዋል።

የእርሻ ጣቢያው በቅርቡ ሥራ ሲጀምር ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የእርሻ ሥራ የልምድ ሽግግር በማድረግ ዞኑን የልማት ቀጠና የማድረግ ተስፋ እንደተጣለበት ጠቅሰዋል።

ሌሎች ባለ ሃብቶች አካባቢውን እንዲያለሙ በመጋበዝና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የልማት አማራጮችን ማስፋፋት ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን አክለዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ በዞኑ ውስጥ ባሉ ሁሉም ቀበሌዎች በግጭት መንስኤዎች ላይ ተደጋጋሚ ውይይት በማድረግ ሰላም ለማስፈን የተደረገው ጥረት ውጤት አሳይቷል ብለዋል።

ችግሮች ሲፈጠሩ ወዲያውኑ የአካባቢውን ባህል መሠረት ያደረገ አቅጣጫ ተሰጥቶ ተግባራዊ እየተደረገ የእርስ በእርስ ኩርፊያዎችን በእርቅ ለመፍታት ተችሏል ነው ያሉት።

በከፍተኛ ጥረት እየተስተዋለ ያለው ይህ አንጻራዊ ሰላም ዘላቂና አስተማማኝ የሚሆነው በአካባቢው መልካም አስተዳደር እና የልማት አማራጮችን መፍጠር ሲቻል መሆኑን አመላክተዋል።

ሰፊ የእርሻ መሬት ያለበት ዞኑ ለክልሉ እና ለሀገር የሚተርፍ ምርት ማምረት እንዲችል እንደቢሮ የፀጥታ ተግባር ላይ ትኩረት በማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የዞኑ ነዋሪዎች የተገኘውን ሰላም በመጠቀም በአካባቢው ያለውን የልማት አማራጭ ወደ ውጤት በመቀየር ረገድ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም