ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የጀመርነውን ተሳትፎ አጠናክረን እንቀጥላለን- የሲቪክ ማህበራት - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የጀመርነውን ተሳትፎ አጠናክረን እንቀጥላለን- የሲቪክ ማህበራት
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 19/2016 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ቁልፍ ሚና ለሚኖረው ሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት የጀመሩትን ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሲቪክ ማሕበራት ገለጹ።
ሀገራዊ ምክክሩ ለረዥም ጊዜ ሲንከባለሉ የቆዩ የግጭት መንስኤዎችና ልዩነቶች ላይ መግባባት ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑንም ማህበራቱ ገልጸዋል፡፡
ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ መምህራን ማሕበር እና የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማሕበር ኮንፌደሬሽን ፕሬዝዳንቶች፤ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር በመተባበር ለምክክሩ ውጤታማነት በትብብር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢዮጵያ መምህራን ማሕበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ዩሐንስ በንቲ እንደገለጹት፤ ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለመገንባት ቁልፍ መፍትሄ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ምክክሩ የግጭት መንስኤ የሆኑ የሀሳብ ልዩነቶችን ወደ አንድ መድረክ አምጥቶ ለመወያየትና እልባት ለመስጠት እንደሚያስችልም ነው የተናገሩት፡፡
በመሆኑም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያገባኛል የሚሉ አካላት በሰከነ መንገድ በመወያየትና የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ገልፀዋል።
ይህን ታሪካዊ አጋጣሚ በመጠቀም ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት በማገዝ በኩል ማሕበሩ የድርሻውን ለመወጣት እየሰራ ነው ብለዋል።
ለአብነትም ማህበሩ ከኮሚሽኑም ጋር የስምምነት ሰነድ ተፈራርሞ በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች አማካኝነት በምክክሩ ላይ ለመሳተፍ እየሰራ እንደሆነም አስረድተዋል።
የኢዮጵያ ሰራተኛ ማሕበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ካሳሁን ፎሎ በበኩላቸው ፤ማህበሩ የምክክር ኮሚሽኑ ከተዋቀረ ጀምሮ የበኩሉን ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ማህበሩ የውይይት ተሳታፊዎች ልየታ ስራ ላይ መሳተፉንም ነው የገለጹት፡፡
በዚህም በክልልና በፌዴራል ደረጃ በምክክሩ ላይ ተሳትፎ የሚያደርጉ አካላትን ለኮሚሽኑ ማሳወቁን ነው የተናገሩት።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ለማልማትና የተጀመረውን የኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠልም የጋራ መግባባት መፍጠር ምትክ የማይገኝለትና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነም አብራርተዋል።
ለሀገራዊ ምክክሩ ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ካሳሁን በመደማመጥ ፣በመግባባትና የሃሳብ ልዩነቶችን አክብሮ ወደ መፍትሔ ለመምጣት ጥረት ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል።
ምክክሩ ለአንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ለወደፊትም ልዩነቶችን በውይይት መፍታት የምንለማመድበት መድረክ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።
የሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ማቋቋሚያ አዋጅ ታሕሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም ማጽደቁ ይታወሳል።