ቀጥታ፡

በበጀት ዓመቱ ከ1 ሚሊዮን በላይ የወተት ላሞች ማዳቀል ተችሏል - የኢትዮጵያ እንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት

አዳማ ፤ ታህሳስ 19/2016 (ኢዜአ)፦ በተያዘው በጀት ዓመት አምስት ወራት  በሰው ሰራሽ ስነ ዘዴ ከ1 ሚሊዮን በላይ የወተት ላሞች ማዳቀል መቻሉን የኢትዮጵያ እንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ እንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አስራት ጤራ ለኢዜአ እንደገለፁት ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት ብዛት ቀዳሚ ብትሆንም ስጋና ወተትን ጨምሮ ከሀብቱ የሚገኘው ምርት እጅግ አነስተኛ ነው።

አገሪቷ በየዓመቱ ከ25 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ በማውጣት ወተትና የወተት ተዋጽኦ ከውጭ የምታስገባ መሆኑንም ለአብነት አንስተዋል።

የሌማት ትሩፋት መርሃግብሩ አምና ይፋ ከሆነ ወዲህ መርሃ ግብሩን ከግብ ለማድረስ ሊተገበሩ ከሚገቧቸው ተግባራት ዋነኛው የወተትና ስጋ ምርት ጥራትና ብዛት መጨመር መሆኑን አክለዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ባለፈው አንድ ዓመት በእንስሳት ዝርያ ማሻሻያና የተሻለ የስጋና ወተት ምርት የሚሰጡ የኮርማ አባለዘር የማምረት ስራ ኢንስቲትዩቱ በትኩረት እየሰራበት ነው።

በዚህም ባለፈው አንድ ዓመት በምርምር የተደገፈ የሀገረሰብ ላሞችና ከውጭ የተገኘ የኮርማ ዝርያ በማምጣት የወተት ላሞች ዝርያ ማሻሻያ ስራ በሰው ሰራሽ ስነ ዘዴ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የሀገሪቷን እንስሳት ምርታማነትና የምርት ጥራት ለማሳደግና ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ ኢንስቲትዩቱ የጥናትና ምርምር ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ በምርምር የተገኙ የኮርማ አባለዘር በማምረት በሰው ሰራሽ ስነ ዘዴ እንዲዳቀሉ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶዝ ማዘጋጀት መቻሉንም አንስተዋል።

በተመሳሳይ አዳቃይ ቴክኒሻኖችን በማሰልጠንና የነባር አዳቃዮችን አቅም በመገንባት በወተት ልማት ላይ በማሰማራት የማዳቀል ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ባለፈው ዓመት ከ1 ነጥብ 2 በላይ የወተት ላሞችን በማዳቀል ከ500 ሺህ በላይ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸውን ጥጆች ማግኘት መቻሉን ጠቅሰው፤ በተያዘው በጀት ዓመት በእስካሁኑ ሂደት ከ1 ሚሊዮን በላይ የወተት ላሞች መዳቀላቸውን ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ የሌማት ትሩፋት መርሃግብሩን ግብ ለማሳካትና በቀጣይነት አጠናክሮ ለማስቀጠል እንዲረዳ  የ10 ዓመት የወተት ልማት ስትራቴጂ ተቀርጾ በቅርቡ ወደ ትግበራ መገባቱን የግብርና ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል።

በዚህም ዩኒቨርሲቲዎች፣ የምርምር ተቋማት፣ በመስኩ የተሰማሩ ድርጅቶች፣ ማህበራትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲጫወቱ የሚያስችል አሰራሮች ተዘርግተው በትብብር እየተሰራ መሆኑም እንዲሁ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም