የአዲስ አበባ ከተማን አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋና ፍትሐዊ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ከተማን አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋና ፍትሐዊ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 19/2016 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማን አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋና ፍትሐዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከህብረተሰቡ ጋር ባካሄዳቸው ውይይቶች ምላሽ እንዲያገኙ ህዝቡ ካቀረባቸው ጥያቄዎች አንዱ ከብልሹ አሰራርና ከሌብነት የጸዳ ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ መሆኑ ተገልጿል።
አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል የከተማ አስተዳደሩ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የከተማው ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ጣሰው ገብሬ ገልጸዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ አገልግሎት አሰጣጡን ከከተማዋ ዕድገትና ከሕዝቡ ፍላጎት ጋር የሚመጣጠን ለማድረግ የዲጂታላዜሽን አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ለውጦች መታየት መጀመራቸውን የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል።
አገልግሎት አሰጣጡን ከብልሹ አሰራር የጸዳና ይበልጥ ቀልጣፋ ለማድረግ የሚያስችል ጥናት ተጠንቶ የአሰራርና የአደረጃጀት ለውጦች መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
በጸደቀው አደረጃጀት መሠረት ብቁ ስነ-ምግባር ያለው የሰው ኃይል ለመፍጠር የክህሎትና የስነ ምግባር ክፍተቶችን መለየትና ክፍተቶቹን የሚደፍኑ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን መስጠት የሚያስችል ምዘና እንደሚካሄድም አስታውቀዋል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው የከተማው ነዋሪ በሚፈልገው መጠን አገልግሎት እያገኘ አለመሆኑን ገልጸው፤ የከተማ አስተዳደሩ የተቋማትን አገልግሎት አስመልክቶ ባካሄደው ጥናትና በተለያዩ ህዝባዊ ውይይቶች አገልግሎቱ መሻሻል እንዳለበት ያሳየ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም ከተፈለገው ክህሎትና የስነ ምግባር ክፍተቶችን መለየትና ክፍተቶችን የሚደፍኑ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን መስጠት የሚያስችል ምዘና እንደሚካሄድ አመራሮቹ ተናግረዋል፡፡
ከዳይሬክተር እስከ ፈጻሚ ድረስ ያሉ ሰራተኞች የሚሳተፉበት ምዘና የፊታችን ቅዳሜ ታህሳስ 20 እንደሚሰጥ የገለጹት የቢሮው ኃላፊው በምዘናው በክህሎትና ስነ ምግባር አንጻር ክፍተት የተገኘባቸው ሰራተኞች በሚመጥኗቸው ቦታዎች ላይ በመመደብ ተገቢው የክህሎትና ስነ ምግባር አቅም ግንባታ ማሻሻያ ስልጠና እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡