ብሔራዊ ባንክ የተረጋጋ የፋይናንስ ስርዓት እንዲፈጠር የሚረዱ ስራዎችን ማጠናከር እንዳለበት ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ብሔራዊ ባንክ የተረጋጋ የፋይናንስ ስርዓት እንዲፈጠር የሚረዱ ስራዎችን ማጠናከር እንዳለበት ተገለጸ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 19/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተረጋጋ የፋይናንስ ስርዓት እንዲፈጠር ለማስቻል የሚረዱ ፈርጀ ብዙ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ።
ቋሚ ኮሚቴው በብሔራዊ ባንክ ተገኝቶ ከባንኩ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱም ባንኩ የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር፣ የውጭ ምንዛሪ አማራጭ ዘርፎችን በማብዛት፣ ጤናማና የተረጋጋ የፋይናንስ ሥርዓት በመዘርጋት፣ የፋይናንስ አካታችነትን ለማሳደግ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት ተገልጿል።
በተጨማሪም ዲጂታላይዜሽንና የቴክኖሎጂ አቅምን ከማጎልበት ፣ በክህሎት የዳበረ የሰው ሀብት ከማፍራት እንዲሁም መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አኳያ ባንኩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባውም ተመላክቷል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጀ ፤ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ከምንጊዜውም በበለጠ ሀገር በቀል የሆኑ የግልና የመንግስት ባንኮች በብዛት በባንክ ኢንዱስትሪው ተሰማርተው ይገኛሉ ብለዋል።
በዚህ የተነሳም ባንኮቹ ገበያው ላይ የሚያደረጉት ውድድር ጤናማ፤ ሕብረተሰቡን እና ሀገርን የሚጠቀም ሆኖ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባው ገልጸዋል።
የዋጋ ንረትን ከመከላከል ፣ የባንኮች የአገልግሎት ክፍያን ከመቆጣጠር እና የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት ከማግኘት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን ከመፍታት አኳያ ብሔራዊ ባንክ እየሰራቸው ያሉ ስራዎችን ለህዝቡ በማሳወቅ ረገድ የሚዲያ አማራጭ ተደራሽነቱን ማስፋት ይገባል ብለዋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ በበኩላቸው የገበያ የዋጋ ንረትን ማርገብ ከባንኩ ቁልፍ ተግባራት ዋነኛው መሆኑን በማስገንዘብ ባንኩ በቅርቡ የወሰዳቸው የገንዘብ ፖሊሲ እርምጃዎች የዋጋ ንረትን በማርገብ፣ የባንክ ብድር ዕድገትን በመግታትና የመንግሥትን የቀጥታ ብድር መጠን በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ አዎንታዊ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከፋይናንስ ጤናማነት መለኪያዎች አንጻር ሲገመገም ከቅርንጫፎች ብዛት፣ ከተቀማጭ የገንዘብ መጠን ፣ በተከፈቱ አካውንቶች ብዛት እና የብድር አሰጣጥ ፤ የፋይናንስ ዘርፉ ጤናማ፣ ትርፋማ እና የተረጋጋ እንደሆነ የባንኩ ገዢ አስረድተዋል፡፡
ሴቶችን አብቅቶ ወደ አመራርነት ከማምጣት፣ ባንኮች የሚሰጡት የአገልግሎት አማራጭ ለአካል ጉዳተኞች ዜጎች ተደራሽ እንዲሆኑ ከማስቻል፣ አኳያ የሚታዩ ክፍተቶችና የተመዘገቡ ጠንካራ ጎኖች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት መካሔዱን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።