አየር መንገዱ ከዳሽን ባንክ ጋር ይፋ ያደረገው  የአየር ትኬት የክፍያ ስርዓት ለደንበኞች መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ነው - አቶ ለማ ያዴቻ 

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 18/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ  አየር መንገድ ከዳሽን ባንክ ጋር ይፋ ያደረገው የረዥም ጊዜ የአየር ትኬት የክፍያ መፈጸሚያ ስርዓት ለተቋማቱም ሆነ ለደንበኞች መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ነው ሲሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ለማ ያዴቻ ገለጹ።

"አሁን ይብረሩ ቆይተው ይክፈሉ" በተሰኘው የጉዞ ክፍያ ሥርዓት መንገደኞች  ከዳሽን ባንክ ጋር ለአጭር ጊዜ በተመቻቸ ብድር የበረራ ትኬት መግዛት ይችላሉ።


 

በረራቸውን ካከናወኑ በኋላ ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በተከፋፈለ ወርሃዊ ክፍያ ተመላሽ እንዲያደርጉ የሚያስችል ሥርዓት መሆኑ ተገልጿል።

አገልግሎቱን ተደጋጋሚ በረራ የሚያካሂዱ ድርጅቶችና ሠራተኞቻቸው፣ በውጭ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎች፣ ለሥራ ወይም ለጉብኝት ወደ ተለያዩ ቦታዎች የሚጓዙ ግለሰቦችና የጉዞ ፈቃድ ያላቸው ሁሉ መጠቀም ይችላሉ ነው የተባለው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ሥራ ዘርፍ  ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለማ ያዴቻ እንደገለጹት፣ የክፍያ ስርዓቱ ለአየር መንገዱም ሆነ ለዳሽን ባንክ ተጨማሪ የደንበኞች ቁጥርን የሚያሰፋ ነው።

በተጨማሪም ተጓዦች ብዙ የገንዘብ መጠን በአንድ ጊዜ መክፈል በማይችሉበት ወቅት በብድር በመጠቀም  ትኬት እንዲገዙ ያስችላቸዋል ነው ያሉት።


 

በዳሽን ባንክ የዲጂታል ባንኪንግ ዘርፍ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዮሐንስ ሚሊዮን በበኩላቸው፣ የክፍያ ስርዓቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ አዲሰ የቢዝነስ እይታ ይዞ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ይህም ሁሉንም ወገኖች ትርፋማ እንደሚያደርግ ነው ያስረዱት። 

የክፍያ ስርዓቱ  የደንበኞችን የመበደር አቅም መሰረት በማድረግ በአንድ ጊዜ እስከ 600 ሺህ ብር ድረስ መበደር እንደሚያስችል ተገልጿል።

ተጓዦች " ፍላይ ጌት" በተሰኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መተግበሪያ አማካኝነት በረራቸውን ማስያዝ እና ከዳሽን ባንክ ባገኙት ብድር ክፍያውን ባሉበት ሆነው መፈፀም እንደሚችሉም ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም