የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህልን ለማዳበር በትኩረት እንደሚሰራ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህልን ለማዳበር በትኩረት እንደሚሰራ ገለጸ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 18/2016(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህልን ለማዳበር በትኩረት እንደሚሰራ ገለጸ።
የጋራ ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ አቶ ሙሳ ፉሮን ሰብሳቢ እንዲሁም አቶ ኪሮስ አጥናፉን ጸሐፊ አድርጎ መርጧል።
አዲሱ ሰብሳቢ አቶ ሙሳ ፉሮ በዚሁ ወቅት፤ ምክር ቤቱ በክልሉ እና በአገር አቀፍ ደረጃ የተሻለ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህልን ለመፍጠርና ብሔራዊ መግባባትን ለማምጣት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ችግሮችንና ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት ባህል እንዲዳብር ቀዳሚ ትኩረቱ አድርጎ እንደሚንቀሳቀስ ጠቁመው፤ በጋራ ጉዳዮች ላይ በመቀራረብ መስራት ይገባል ነው ያሉት።
በስብሰባው የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በበኩላቸው፤ በአገሪቱ የፖለቲካ ባህል እንዲዳብር በጋራ መስራት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገር ጥቅምና ለህዝብ አንድነት መጠናከር ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባቸው የገለጹት፤ የአርጎባ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አቶ መሐመድ ሙሳ ናቸው።
የኢትዮጵያ ብሔር አንድነት ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚሃብሔር፤ ከልዩነት ይልቅ አብሮነትና ትብብር ላይ በማተኮር የተሻለች አገር ለመገንባት ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት ብለዋል።
የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሁሉንም ጥረት የሚጠይቅ በመሆኑ ፓርቲዎች ገንቢ ሚና መጫወት አለባቸው ያሉት ደግሞ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ ናቸው።
የሰለጠነ እና አሻጋሪ የፖለቲካ አመለካከትን በመከተል ነገን የተሻለ ለማድረግ መትጋት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የገዳ ቢሊሱማ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ መሳይ አበበ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አጋዥ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል።