በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጾታዊ ጥቃቶችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እንዲጠናከር ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጾታዊ ጥቃቶችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እንዲጠናከር ተጠየቀ
ጋምቤላ፤ ታህሳስ 18/2016 (ኢዜአ) በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጾታዊ ጥቃቶችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ መጠናከር እንዳለበት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
"በየትም፣ የትም፣ በምንም ሁኔታ ጾታዊ ጥቃትን ዝም አንልም'' በሚል መሪ ሀሳብ ለሁለት ሳምንታት ሲካሄድ የቆው የፀረ ፆታዊ ጥቃት ዘመቻ ማጠቃለያ መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ክልል እየተካሄደ ነው።
የሴቶችና ሕጻናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ በመድረኩ እንዳሉት፣ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እና ጾታዊ ጥቃቶች ለአካልና ለስነ ልቦና ጉዳት ይዳርጋሉ።
ከእዚህም በተጨማሪ ሴቶችና ሕጻናትን ድርብርብ ለሆኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየዳረጉ መሆናቸውን ነው ያስረዱት።
ኢትዮጵያም ጾታን መሠረት በማድረግ የሚፈጸም ጥቃትን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት ለችግሩ የተጋለጡ ሴቶችና ህጻናት ህይወታቸውን በዘላቂነት ለመታደግ እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።
ለእዚህም የተቀናጀና ዘርፈ ብዙ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ተቋማት የማቋቋም፣ የማጠናከርና ለአገልግሎት የማዘጋጀት ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታዋ።
ተገቢ ምላሽ ለመስጠት የሚያግዙ ህጎችንና ፖሊሲዎችን ከማውጣት ባለፈ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ስምምነቶችን የኢትዮጵያ የህግ አካል በማድረግ ለተፈጻሚነቱ በትኩረት እየሰራች መሆኑንም ነው የገለጹት።
እንደ ወይዘሮ አለሚቱ ገለጻ፣ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግና ጥቃትን ለማስወገድ ሚኒስቴሩ በተዋረድ ከሚገኙ የክልልና የከተማ አስተዳደር ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮዎች ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው።
በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃቶች እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት እየተከናወኑ ላሉ ሥራዎች ስኬታማነት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብር መጠናከር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የዘመቻው ዋና ዓላማም ጾታዊ ጥቃት የሚያስከትለው አሉታዊ ተጽዕኖ ላይ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ግንዛቤ ለመፍጠርና ድርጊቱን ለማስቆም መሆኑንም አስታውቀዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው ፆታዊ ጥቃት በሴቶችና ህፃናት ላይ ከሚያስከትለው ጉዳት በተጨማሪ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ጨምሮ ለሌሎች ተላላፊ በሽታዎች እንደሚያጋልጥ ተናግረዋል።
ፆታዊ ጥቃት አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑን በመገንዘብ በየአካባቢያችን የሚፈፀሙ ያለ ዕድሜ ጋብቻ፣ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት የክልሉ መንግስት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ክርምስ ሌሮ በበኩላቸው፣ መድረኩ ጾታዊና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ይበልጥ እንዲጠናከሩ ያግዛል ብለዋል።
በመድረኩ ላይ በዘመቻው የተሰሩ ሥራዎች ሪፖርት ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት እየተደረገበት ሲሆን፣ የሁሉም ክልሎች ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊዎች፣ የሚኒስቴሩ ተወካዮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።