አየር መንገዱ "አሁን ይብረሩ ቆይተው ይክፈሉ" የሚል የጉዞ የክፍያ ሥርዓት ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
አየር መንገዱ "አሁን ይብረሩ ቆይተው ይክፈሉ" የሚል የጉዞ የክፍያ ሥርዓት ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 18/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ከዳሽን ባንክ ጋር የአውሮፕላን ቲኬት ክፍያን ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ለመፈጸም የሚያስችል " አሁን ይብረሩ ቆይተው ይክፈሉ " የሚል የጉዞ ክፍያ ሥርዓት ይፋ አደረገ።
"አሁን ይብረሩ ቆይተው ይክፈሉ" የሚል የጉዞ ክፍያ ሥርዓት ደንበኞች ከዳሸን ባንክ ጋር ለአጭር ጊዜ በተመቻቸ ብድር ተጠቃሚ ይሆናሉ።
ደንበኞች የበረራ ቲኬታቸውን ገዝተው በረራቸውን ካከናወኑ በኋላ ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ክፍያውን እንዲፈጽሙ የሚያደርግ ሥርዓት መሆኑ ተገልጿል።
አገልግሎቱን ተደጋጋሚ በረራ ለሚያካሂዱ ድርጅቶች፣ ሠራተኞቻቸው፣ በውጭ ንግድ ለተሰማሩ ነጋዴዎች፣ ለሥራ ወይም ለጉብኝት ወደ ተለያዩ ቦታዎች ለሚጓዙ ግለሰቦችና የጉዞ ፈቃድ ያለው ሁሉ የሚያገኙ ይሆናል።
በዚህም ተጓዦች "ፍላይ ጌት" በተሰኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መተግበሪያ አማካኝነት በረራቸውን ማስያዝ እና ከዳሽን ባንክ ባገኙት ብድር ክፍያውን ባሉበት ሆነው መፈፀም እንደሚችሉም ታውቋል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ሥራ ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለማ ያዴቻ፤ በዳሽን ባንክ የዲጂታል ባንኪንግ ኃላፊ ዮሐንስ ሚሊዮን እና ሌሎችም የተቋማቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።