ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚያገለግል የቆጣሪ ውል እድሳት ጀምሯል

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 18/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚያገለግል የቆጣሪ ውል እድሳት ማድረግ ጀምሯል።

ይህን ተከትሎ ከኅዳር 1 እስከ ታኅሣሥ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ 100 ሺህ ደንበኞች ውላቸውን ማደሳቸውን አገልግሎቱ አስታውቋል፡፡

ተቋሙ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማዘመን በማሰብ ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚያገለግል የቆጣሪ ውል እድሳት እያደረገ ይገኛል። 

የውል እድሳት ዓላማው ለደንበኞች ቀልጣፋ አገልግሎትና ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች በቀላሉ ምላሽ መስጠት ነው ተብሏል።

የውል እድሳቱ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ቆጣሪዎችን ለማወቅና አዳዲስ ቆጣሪዎችን ለደንበኞች ለመስጠት እንደሚያስችል ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር መላኩ ታዬ፤ የውል እድሳቱ ዓላማ ደንበኞችን በሚገባ ማወቅና የደንበኞችን ፍላጎት መሠረት ያደረገ አገልግሎት መስጠት ነው።

ቆጣሪን ለማይታወቅ አካል የሚያስተላልፉ ደንበኞችን ለመቆጣጠርና የኃይል ሥርቆትን ለማስቀረት እንዲሁም  የኃይል መቆራረጥ ችግር ለማቃለል እንደሚያስችል አመልክተዋል።

ደንበኞች እስከ መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ በተቋሙ ቅርንጫፎች በመገኘት ውላቸውን እንዲያድሱ ነው አቶ መላኩ ያሳሰቡት።

ውል ከፈፀሙ አምስት ዓመት የሞላቸው ደንበኞች  እንዲያድሱ  የሚገደዱ ሲሆን፤ አዲስ የሚያድሱት ውል ደግሞ ለአምስት ዓመት የሚቆይ እንደሆነ አብራርተዋል።

ኢዜአ የውል እድሳቱን በተመለከተ የአገልግሎቱን ተጠቃሚዎች አነጋግሯል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት አቶ ሳሙኤል ነጋሽ፣ ወይዘሮ ሐና ዘሪሁን እና አቶ እንዳለ ክንፈ የውል እድሳት አገልግሎቱን ለማግኘት በሄዱባቸው ቅርንጫፎች ሁሉ ያለ ምንም እንግልት መስተናገዳቸውን ጠቅሰዋል። 

የደንበኞች የክፍያ አገልግሎት በባንኮችና በቴሌብር የሚሰጠው በነፃ ቢሆንም አንዳንድ ግለሰቦች   በ"ዲጂታል እንክፈልላችሁ" በሚል እያጭበረበሩ እንደሚገኙ የገለጹት አቶ መላኩ፤ ደንበኞች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም