ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል የ1 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ከአፍሪካ ህብረት ጋር ተፈራረመች

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 18/2016(ኢዜአ)፦ የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል የ1 ሚሊዮን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ከአፍሪካ ህብረት ጋር ተፈራርሟል።

ገንዘቡ በፕሪቶሪያ በተፈረመው ስምምነት መሰረት ለሚከናወነው የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለመቋቋም የሚከናወኑ ስራዎችን ለማገዝ እንደሚውል ተመላክቷል።

ስምምነቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በተገኙበት የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽነር አምባደር ተሾመ ቶጋ ከአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ፣ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ኮሚሽነር ባንኮሌ አዲዮ ጋር ተፈራርመዋል።

በፊርማ ስርዓቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የአፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።


 

የአፍሪካ ህብረት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የነበረውን ሚና የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው ህብረቱ በዛሬው እለት ከኮሚሽኑ ጋር ያደረገው የድጋፍ ስምምነት የመልሶ ማቋቋም ስራዎች እንዲከናወኑ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ፣ ሰላምና ደህንነት ጎዳዮች ኮሚሽነር ባንኮሌ አዲዮ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ለመተግበር ያለውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።


 

የዛሬው ስምምነትም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ህብረት የሰላም ፈንድ ተጠቃሚ በመሆን በአህጉሪቱ የመጀመሪያዋ ሀገር ያደርጋታል ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት ዘላቂ ሰላምን በኢትዮጵያ ለማረጋገጥ ከሀገሪቱ ጋር ተቀራርቦ መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ የአፍሪካ ህብረትን አመስግነው ኮሚሽኑ ድጋፉ ለሚገባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲደርስ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

አምባሳደር ተሾመ ሌሎች አጋር አካላትም የመልሶ ማቋቋሙን ስራ እንዲደግፉ ጥሪ ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም