ቀጥታ፡

ሕገ-ወጥ ንግድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የንግድና ዘርፍ ማኅበራትና የመንግሥት ቅንጅታዊ አሠራር መጠናከር አለበት

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 18/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የሚስተዋለውን ሕገ-ወጥ ንግድ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የንግድና ዘርፍ ማኅበራትና የመንግሥት ቅንጅታዊ አሠራር መጠናከር እንዳለበት ተገለጸ።

በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አዘጋጅነት ሕገ-ወጥ ንግድን መከላከል ላይ ያተኮረ አገር አቀፍ ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል። 


 

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ፍስሐ ይታገሱ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ መንግሥት ከኢኮኖሚ ፖሊሲ አኳያ ግልጽነት እና ወጥነት ያለው የአሠራር ሥርዓት ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።

በተለይም በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማጉላት በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

ይሁን እንጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ብሎም እድገት እየጎዳው ይገኛል።

በተጨማሪም ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞ እንቅፋት ስለመሆኑም አንስተዋል።

በመሆኑም መንግሥት ሕገ-ወጥ ንግድን ለመግታት የተለያዩ የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓቶችን ዘርግቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

ነገር ግን የግሉ ዘርፍና የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ትብብርና ጠንካራ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት በሁሉም ዘርፎች ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።

በተለይም መድኃኒት፣ የቁም እንስሳትና አልባሳት ዋነኞቹ ለሕገ-ወጥ ንግድ የተጋለጡ ዘርፎች ስለመሆናቸው አብራርተዋል።

ሕገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል የሎጂስቲክስና የሕግ ማዕቀፎችን በአግባቡ መምራትና ማስፈፀም ያስፈልጋል ብለዋል።

መንግሥት የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማጎልበት የተለያዩ የማሻሻያ ሥራዎችን ተግባራዊ እያደረገ ቢሆንም በሕገ-ወጥ ንግድ የሚሳተፋ ነጋዴዎችን ለይቶ ተጠያቂ ማድረግ ላይ ክፍተቶች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በሕገ-ወጥ በአሠራሮች ላይ ያሉ ክፍተቶችን ነቅሶ በማውጣት ተጠያቂነት እንዲሰፍን ማድረግ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም