የቁልቢ ገብርኤል በዓል በሰላም እንዲከበር በቂ ዝግጅት ማድረጉን የጋራ ግብረ-ኃይሉ ገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
የቁልቢ ገብርኤል በዓል በሰላም እንዲከበር በቂ ዝግጅት ማድረጉን የጋራ ግብረ-ኃይሉ ገለፀ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 18/2016(ኢዜአ)፦ የቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓል በሰላም እንዲከበር የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል በቂ ዝግጅት ማድረጉን ገለፀ።
የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ሜታ ወረዳ የሚከበረው የቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓል በሰላም እንዲከበር በቂ ዝግጅት ማድረጉን ገልጿል።
ታህሳስ 19 ቀን 2016 ዓ.ም የሚከበረው የቁልቢ ገብርኤል ክብረ በዓል በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ከአካባቢው አስተዳደር፣ ከሀይማኖት አባቶች እና ከኅብረተሰቡ ጋር በመተባበር በቂ ዝግጅት አድርጎ ስምሪት ወስዶ ወደ ተግባር መግባቱን በመግለጫው አስታውቋል፡፡
የአካባቢው ኅብረተሰብ ለበዓሉ ታዳሚዎች ቅድሚያ በመስጠት የተለመደውን የእንግዳ ተቀባይነት ባህሉን በማሳየት ቀና ትብብር እንዲያደርግ የጋራ ግብረ -ኃይሉ ጠይቋል፡፡
የበዓሉ ታዳሚዎችና ኀብረተሰቡ ለፀጥታ ስጋት የሆኑ አስጊ ሁኔታዎችን ሲመለከት በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች በፍጥነት ጥቆማ በመስጠት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ የጋራ ግብረ -ኃይሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡