በክልሎቹ በመኸር ወቅት የለማውን ሰብል ብክነትን በመቀነስ ለመሰብሰብ ኮምባይነሮች ጥቅም ላይ ውለዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሎቹ በመኸር ወቅት የለማውን ሰብል ብክነትን በመቀነስ ለመሰብሰብ ኮምባይነሮች ጥቅም ላይ ውለዋል

ሆሳዕና/ዲላ/ቦንጋ ፤ ታህሳስ 18/2016(ኢዜአ)፡ በደቡብ፣ በማዕከላዊና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች በ2015/16 የመኸር ወቅት የለማ ሰብልን ለመሰብሰብ ኮምባይነሮችን ጨምሮ ሌሎች ዘዴዎችን መጠቀማቸውን የየክልሎቹ ግብርና ቢሮዎች ገለጹ።
የደረሰ ሰብልን በዘመናዊ የአሰባሰብ ዘዴን ኮምባይነሮች ጭምር ታግዞ በማንሳት የምርት ብክነትን ከመከላከል ባለፈ ሰብልን ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ መታደግ መቻሉም ተመላክቷል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መላኩ ባፋ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት ለመሰብሰብ ከደረሰ 310 ሺህ 879 ሄክታር ማሳ ሰብል ውስጥ ከ284 ሺህ 140 ሄክታር በላይ የሚሆነውን ማንሳት መቻሉን ጠቅሰዋል።
ከዚህም ውስጥ ከ12 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን አስረድተዋል።
በተለይ በኩታ ገጠም ከለማ 41 ሺህ 269 ሄክታር መሬት ላይ የለማውን የስንዴ እርሻ 282 ኮምባይነሮችን በማሰማራት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሚደርስ ምርት መሰብሰብ መቻሉንም ተናግረዋል።
በዚህም ሰብሉን ከምርት ብክነትንና ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ መታደግ መቻሉንም ጠቅሰዋል።
ቀሪውን የደረሰ ሰብል በአጭር ጊዜ ውስጥ በመሰብሰብ ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለመከላከል የሰው ሀይልንና ሌሎች ዘዴዎችንም በተቀናጀ መንገድ ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
እስካሁን 254 ሺህ ሄክታር ላይ የነበረ ሰብል ማንሳት መቻሉንና ከ22 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ የእርሻ ዘርፍ ሃላፊ አቶ አድማሱ አወቀ ናቸው።
679 ሄክታር መሬት ላይ የለማ ስንዴ በኮምባይነር የማንሳት ስራ የተከናወነ ሲሆን ከዚህም ከ20 ሺህ በላይ ኩንታል ምርት መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።
በክልሉ በርካታ የመኸር ሰብል አልተሰበሰበም ያሉት ሃላፊው በተለይ በኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ አሌና ጋርዱላ አካባቢዎች በቆሎና ማሽላን ጨምሮ ሌሎች የአገዳ ሰብሎች አለመድረሳቸውን አስረድተዋል።
በወላይታና ጋሞ እንዲሁም ጌዴኦ አካባቢዎች የደረሱ ቋሚና የአዝዕርት ሰብሎችን የማንሳቱ ተግባር በልዩ ትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
የደረሰ ሰብልን በአጭር ጊዜ በማንሳት ምርትን ተገማች ካልሆነ የአየር ለውጥና ከተባይ ለመከላከል አርሶ አደሩና በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በክልሉ ጌዴኦ ዞን የራጴ ወረዳ የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አማኑኤል ወርቁ በበኩላቸው ከ637 ሺህ 884 ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቅሰው እስካሁን ሃምሳ በመቶውን ማንሳት መቻሉንም አስረድተዋል።
በተያያዘም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በመኸር ወቅት በዘር ከተሸፈነው 328 ሺህ 400 ሄክታር በላይ ማሳ ውስጥ ከ230 ሺህ ሄክታር በላይ የደረሰ ሰብል መሰብሰቡን የግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አሸናፊ ክንፉ ገልጸዋል።
በአጠቃላይ ለመሰብሰብ ከታቀደው ከ7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እስከአሁን ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ገልፀዋል።
በመኸር አዝመራ አርሶ አደሩ የተሻለ ምርት ያገኘ ቢሆንም ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብና ቅዝቀዜ ምክንያት ምርት ላይ ጉዳት እንዳያስከትል የደረሱ ሰብሎችን በተደራጀ አግባብ በመሰብሰብ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የደረሱ የአትክልት፣ የፍራፍሬና ሌሎች የሆርቲካልቸር ምርቶች በርጥብነታቸው የሚሰበሰቡ በመሆኑ ብዙም ችግር አለመኖሩን ገልጸዋል።
ቢሮው በድህረ ምርት ወቅት የሚከሰተውን የምርት ብክነት ለመከላከል ግንዛቤ ማስጨበጥና ስልጠናን ጨምሮ የምርት ማከማቻ ፒክስ ከረጢቶችን ለአርሶ አደሩ የማከፋፈልና ዘመናዊ የብረት ጎተራን በተመረጡ 11 ወረዳዎች የማስተዋወቅ ስራ እየሰራ ነውም ብለዋል።
ምርቱን ከመሰብሰብ ባለፈ የምርት ብክነት እንዳይከሰት በአሰባሰብ፣ በውቂያና በማከማቸት ወቅት ተገቢ ጥንቃቄ እንዲደረግ በየደረጃው የሚገኘው አመራር እና የግብርና ባለሙያዎች ለአርሶ አደሩ ተገቢውን ድጋፍ እና ክትትል እንዲያደርጉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።