157 የኢንዱስትሪ ፓርክ የማምረቻ ሼዶች ወደ ስራ ገብተዋል - የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን - ኢዜአ አማርኛ
157 የኢንዱስትሪ ፓርክ የማምረቻ ሼዶች ወደ ስራ ገብተዋል - የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 18/2016(ኢዜአ)፦ 157 የኢንዱስትሪ ፓርክ የማምረቻ ሼዶች በባለሀብቶችና በአምራች ኩባንያዎች አማካኝነት ወደ ስራ መግባታቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ እንደተናገሩት ከዚህ ቀደም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ስር የሚተዳደሩ አብዛኛዎቹ ሼዶች በባለሀብቶች ያልተያዙ ነበሩ።
ባለፈው አንድ አመት ኮርፖሬሽኑ ባከናወነው ጠንካራ የሪፎርም ስራ በኮርፖሬሽኑ ከሚተዳደሩ 177 የማምረቻ ሼዶች መካከል 157ቱ በባለሀብቶችና በአምራች ኩባንያዎች ተይዘዋል ብለዋል።
የቀሩት 20 ሼዶችም በአዳዲስ ኢንቨስትመንቶች የመያዝ ምጣኔያቸው ከፍ እንዲል በከፍተኛ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኮርፖሬሽኑ በተሠራው የገበያ ማፈላለግና ጠንካራ የድጋፍና ክትትል ስራ በሀገሪቱ ከሚገኙ 13 ኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ነጻ የንግድ ቀጣና መካከል አምስቱ ሙሉ በሙሉ በኢንቨስተሮች መያዛቸውን ጠቁመዋል።
በአዳማ ፣ በቦሌ ለሚ ፣በሰመራ እና በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣና የማምረቻ ሼዶች ሙሉ በሙሉ በአልሚዎች መያዛቸውን አስታውቀው ፤ በሰመራና በሌሎች ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ያልገቡ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ የተቀናጀ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ኮርፖሬሽኑ በአውሮፓ ፣ በደቡብ አሜሪካ ፤ በእስያና በሌሎች አህጉራት የሚገኙ ገበያዎችን የሚከታተል ቡድን አዋቅሮ ኢንቨስተሮችን የማፈላለግ ሥራ እያከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።
በ2015 እና በ2016 በጀት ዓመት እስካሁን ወደ ሥራ ለመግባት ከተፈራረሙ 53 ባለሀብቶችና አምራች ኩባያዎች መካከል 50 በመቶ በላይ የሚሆኑት የሀገር ውስጥ አምራቾች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በመላው ሃገሪቱ በሚገኙ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ100 ሺ በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች የግብርና ምርቶችን ለማቅረብ የገበያ ትስስር መፍጠር ተችሏል ብለዋል፡፡
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ከ100 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩንም አንስተዋል።