የቴክኒክና ሙያ ተቋማቱ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ለኢንተርፕራይዞች ሊያሸጋግሩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቴክኒክና ሙያ ተቋማቱ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ለኢንተርፕራይዞች ሊያሸጋግሩ ነው
ሆሳዕና ታህሳስ 18/2016 (ኢዜአ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙት ሁለት የቴክኒክና ሙያ ተቋማት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከማፍለቅ ባሻገር ፤በገቢ ራሳቸውን ለመቻል ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ገለጹ።
ኮሌጆቹ በ20 ዓመታት ውስጥ ራስ ገዝ ለመሆን የተያዘውን ግብ ለማሳካት እየሰራን ነው ብለዋል።
የሆሳዕናና የዱራሜ ፖሊ ቴክኒክና ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች ኃላፊዎች ለኢዜአ እንደተናገሩት በተሰማሩባቸው የሙያ መስኮች ከሚያፈሩት የሰው ኃይል በተጨማሪ ራሳቸውን የሚያስችላቸው ገቢ ለማግኘት መሥራት ጀምረዋል።
የሆሳዕና ፖሊ ቴክኒክ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ ዲን አቶ አወል ሸንጎ ኮሌጁ የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግሮች በቀላሉ ለመፍታትና ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማፍለቅና ለማሸጋገር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
"በኮሌጁ መምህራን በግብርናው ዘርፍ ፀረ አረም መርጫ፣ የመኖ መከትከቻ፣ የግዙፍ ማሽነሪዎች ማንሻን ጨምሮ ሌሎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማፍለቅ ችለናል፤ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችም ለማሸጋገር በሂደት ላይ እንገኛለን" ብለዋል።
ኮሌጁ ቴክኖሎጂን በማሸጋገር ገቢ ማመንጨት መጀመሩንና ሥራውንም አጠናክሮ በማስቀጠል በረጅም ጊዜ በገቢው የሚተዳደር ተቋም ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ዲኑ ተናግረዋል።
የዱራሜ ፖሊ ቴክኒክ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ ዲን አቶ ደሳለኝ አኔ በበኩላቸው ኮሌጁ አዳዲስ የፈለቁ ቴክኖሎጂዎችን ከማሸጋገር ባለፈ፤ ገቢ ለማመንጨት ባደረገው እንቅስቃሴ በሦስት ሄክታር መሬት ላይ የእርሻ ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የተሽከርካሪዎች ጥገና የሚያከናውንበት ጋራዥ በማቋቋም በአጭር ጊዜ ውስጥ ራሱን በገቢ ለመደገፍ እንደሚሰራም ገልጸዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያዊ ክልል የትምህርትና ስልጠና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የቴክኖሎጂ ሽግግርና ኢንዱስትሪ ትስስር ዘርፍ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ሙስጠፋ ኢሳ የክልሉ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት በተለያዩ ሙያና ክህሎት የበለፀጉና ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ዜጐችን እያፈሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና መስጫ ማዕከላት የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን የምርት ብክነትን ለመከላከል የሚያስችሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
መንግሥት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች በቀጣይ 20 ዓመታት ራስ ገዝ እንዲሆኑ አቅጣጫ ማስቀመጡን ተከትሎም በክልሉ የሚገኙ ተቋማት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን አቶ ሙስጠፋ አስታውቀዋል።
በክልሉ 37 የፖሊ፣ ኢንዱስትሪያልና ኮንስትራክሽን ኮሌጆች ያሉ ሲሆን፣ ዘንድሮ ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብለው በማሰልጠን ላይ እንደሚገኙም መረጃዎች ያሳያሉ።