ቀጥታ፡

በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የወተት ላም እርባታ ስራው ውጤታማ ስላደረገን ህይወታችን እየተለወጠ ነው - የወንዶ ገነት ወረዳ አርሶ አደሮች

ሀዋሳ ፤ ታኀሣሥ 18/2016(ኢዜአ):-  በሲዳማ ክልል ወንዶ ገነት ወረዳ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በወተት ላም እርባታ የተሰማሩ አርሶ አደሮች  በወተት ሽያጭ ከሚያገኙት ገቢ ኑሯቸው እየተለወጠ መምጣቱን ተናገሩ ።

በክልሉ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ከ56 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማደራጀት በወተት ላሞች እርባታ ስራ ላይ እንዲሰማሩ መደረጉ የተገለፀ ሲሆን ከአንዲት ላም የሚገኘውን ወተት በሊትር ከ25 እስከ 30 ማድረስ መቻሉም ተጠቁሟል።

በክልሉ ወንዶ ገነት ወረዳ ወሻና ሶያማ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ሰንበቶ ሙዲ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ቀደም ሲል የነበሯቸውን ላሞች ዝርያ በማሻሻል ከአንድ ላም ያገኙት የነበረውን በቀን 10 ሊትር ወተት በአሁኑ ወቅት ወደ 28 ሊትር ማድረስ ችለዋል።

ሶስት አይነት ዝርያ ያላቸው 30 ላሞች እንዳሏቸው የተናገሩት አርሶ አደሩ ከነዚህ ላሞች በቀን ከ200 ሊትር በላይ ወተት እንደሚያገኙ ተናግረዋል።

ወረዳው ከኦሮሚያ ክልል ጋር የሚዋሰን በመሆኑ የገበያ ችግር እንዳልገጠማቸው አንስተው በሌማት ትሩፋት መርሃግብሩ በወተት ላም እርባታ ተሰማርተው ውጤታማ በመሆናቸው ህይወታቸው እየተቀየረ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህን ስራ በማስፋት የላሞቻቸውን ቁጥር 80 ለማድረስ የላሞች በረት እየገነቡ መሆኑንም አክለዋል።

ከዚህ ቀደም ከነበሯቸው ሁለት ላሞች በቀን ከ10 ሊትር ያልበለጠ ወተት ያገኙ እንደነበር ያስታወሱት በወረዳው ወተራና ቀጨማ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ደስታ ዮሴፍ አሁን ላይ ላሞቹን በተሻሻለ ዝርያ የወተት ላሞች ተክተው ቁጥራቸውን ማድረሳቸውን ገልጸዋል።

ከነዚህ ላሞች አምስቱ የሚታለቡ ናቸው ያሉት አርሶ አደሩ ከአንድ ላም በቀን ከአስራ አምስት እስከ ሀያ ሊትር ወተት እንደሚያገኙና ወተቱን በመሸጥ ቤተሰቦቻቸውን እያስተዳደሩም መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አሰለፈች አሰፋ በበኩላቸው በአንድ የሀበሻ ላም የጀመሩት ስራን በማስፋትና ዝርያ በማሻሻል በአሁኑ ሰዓት 14 ማድረስ እንደቻሉ ተናግረዋል።

በዚህም ልጆቻቸውን በሙሉ ዩኒቨርሲቲ አስተምረው በማስመረቅ ስራ እንደያዙላቸውና በወተት ልማቱ ስራም ለአራት ሰዎች የስራ ዕድል እንደፈጠሩም ገልጸዋል።

የወንዶ ገነት ወረዳ እንስሳት ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊና የኤክስቴንሽን ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ኢሳያስ ያበረ እንዳሉት፤ በወረዳው በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ከ3 ሺህ 120 በላይ አርሶ አደሮች በ30 የወተት መንደር ተደራጅተው ተሰማርተዋል።

የሌማት ትሩፋት ተግባራዊ ለማድረግ በተጀመረው ንቅናቄም በወረዳው አምስት ፓኬጆች ተለይተው ወደ ስራ እንደተገባ የጠቆሙት ኃላፊው ከነዚህ ውስጥ የወተት ላም ዝርያ የማሻሻልና የመኖ ልማት ዋናዎቹ እንደሆኑም ጠቁመዋል።

የክልሉ እንስሳትና አሳ ሀብት ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ተክሌ ጆምባ በበኩላቸው በክልሉ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ወደ ተግባር በተገባው መሰረት በመንደር በማደራጀት ነዋሪው ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።


በዚህም በክልሉ በወተት መንደር በ22 ወረዳዎች የሚገኙ 157 ቀበሌዎች ተለይተው መደራጀታቸውን ገልጸው በነዚህ ቀበሌዎች የሚገኙ ከ56 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማደራጀት የወተት ላሞች እርባታ ስራ መጀመሩን  ገልጸዋል።

በዚህም ከአንድ ላም የሚገኘውን የወተት ምርት መጠን ከ25 እስከ 30 ሊትር ማድረስ መቻሉንም ተናግረዋል።

በተያዘው ዓመት 155 ሺህ ላሞችን ዝርያ ለማሻሻል እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው ከዝርያ ማሻሻል ስራው ጎን ለጎን የመኖ ልማት ስራውም ቀጥሎ ከ20 ሺህ 966 ሄክታር በላይ መሬት በመኖ እፅዋት እንዲለማ መደረጉን ገልጸዋል።

የወተት ምርቱ የገበያ እጥረት እንዳይገጥመው ከይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርክ እንዲሁም በከተሞች ለተጠቃሚው ማህበረሰብ የሚያደርሱ ማህበራትን በማደራጀት ለገበያ እየቀረበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ አመቱ 318 ሺህ ቶን ወተት ከክልሉ በመሰብሰብ ለገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ 153 ሺህ 472 ቶን ወተት መሰብሰብ እንደተቻለም ቢሮው አስታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም