የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተሳታፊዎችን መለየት የሚያስችል ስልጠና በጅማ ከተማ እየሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተሳታፊዎችን መለየት የሚያስችል ስልጠና በጅማ ከተማ እየሰጠ ነው
ጅማ፤ ታኀሣሥ 18/2016(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተሳታፊዎችን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መለየት የሚያስችል ስልጠና ለተለያዩ ህብረተስብ ክፍሎች በጅማ ከተማ እየሰጠ ይገኛል።
በስልጠና መርሃግብሩ ላይ ከ7 ዞኖችና ከአራት የከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ 791 የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳፉ ነው።
ለሀገራዊ የምክክር መድረኩ ትክክለኛ እና ወካይ ተሳታፊ አካላትን ለመለየት ታልም በተዘጋጀው ስልጠና ላይ የፖለቲካ ፖርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ አባ ገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች፣ የፍትህ አካላትና የወጣቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር አምባዬ ኦጋቶ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ሀገራዊ ምክክሩ አለመግባባቶችን በመወያየት እና በመነጋገር ለመፍታት አልሞ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ነው።
''የትኛውንም ችግሮቻችንን በመነጋገር እና በመወያየት ለመፍታት መስራት እና ይህንኑ ተነጋግሮ የመግባባት ባህላችንን ማጎልበትም ሌላው ትልቁ ግቡ ነው'' ብለዋል።
በዚህ ስልጠና መድረክ ላይ የሚሳተፉ የማህበረሰብ ክፍሎች ለችግሮች መፍትሔ የሚያመላክቱ አካላትን ከመምረጥ አኳያ ትልቅ ሀገራዊ አደራ ተጥሎባችኋል ነው ያሉት።
በተለያዩ ክልሎችና ከተሞች ተሳታፊ አካላትን የመለየት ስራው እየተሰራ እንደሆነ የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ ቀሪ ስራዎችም ጎን ለጎን እየተከናወኑ እንደሆነ ተናግረዋል።
ሌላው የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር ዘገዬ አሰፋው በበኩላቸው ''የምናደርገው ምክክርና ውይይት ችግር ፈቺ እንዲሆን ግልጽና እውነተኛ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ መሆን ይገባዋል'' ብለዋል።
''ሀገራችንን ከሰላም እጦት ለማውጣት የተለያየ ጥያቄ ያላቸው አካላት ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመጡ መጠየቅ እና ለሀገር መረጋጋት በጋራ መስራት አለብን'' ሲሉም አክለዋል።
በኮሚሽኑ የስልጠና መርሃግብር ላይ የጅማ፣ የቡኖ በደሌ፣ የኢሉባቡር ፣ የቄለም ወለጋ ፣ሆሮ ጉድሩ ወለጋ፣ ምእራብና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች እና ከጅማ፣ ከአጋሮ፣ ከመቱና ከነቀምቴ የከተማ አስተዳደሮች የመጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
ዛሬ በጅማ ከተማ የተጀመረው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የተሳታፊ አካላትን ለመምረጥ የሚያስችል የስልጠና መርሃግብር ለሶስት ቀናት የሚቆይ ይሆናል።