አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመውሊድ በዓልን ትውፊታዊ የአከባበር ስርዓትን ሊያጠና ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመውሊድ በዓልን ትውፊታዊ የአከባበር ስርዓትን ሊያጠና ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 17/2016(ኢዜአ)፦አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመውሊድ በዓል ትውፊታዊ የአከባበር ስርዓትና ባህላዊ ገፅታን ለመሰነድ የሚያስችል ጥናት ሊያካሂድ ነው።
ጥናቱን የሚያካሂደው በዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ባህሎች አካዳሚ ሲሆን፥ የእምነቱ ተከታዮች፣ ምሁራንና ሌሎች አካላት በተገኙበት የጥናት ማስጀመሪያ ፕሮጀክት ለመቅረፅ ያለመ ውይይት ተካሂዷል።
የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አብዱራዛቅ መሀመድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የመውሊድ በዓል በኢትዮጵያ በአዋጅ ጸድቀው ከሚከበሩ የሃይማኖት በዓላት አንዱ ሲሆን መከበር ከጀመረም 50 ዓመታትን አስቆጥሯል።
አካዳሚው የበዓሉን ባህላዊ ገጽታ በጥናት ማሳየት፣ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የመውሊድን በዓል ሲያከብሩ በበዓሉ ቀንና ከበዓሉ በኋላ የሚተገብሯቸውን ስርዓቶች ከባህል ጥናት አንጻር ምን እንደሚመስሉ ለማጥናት ማቀዱን ተናግረዋል።
የጥናት ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ሊወስድ እንደሚችል ተገልጿል።
ዶክተር አብዱራዛቅ እንዳሉት በጥናቱ የበዓሉ ታዳሚዎች በሚያከናውኗቸው ተግባራት ውስጥ ያሉ አገር በቀል ዕውቀቶች ይፈተሻሉ።
የበዓሉ ባህላዊ መልክ ለማህበራዊ ግንኙነት፣ ለአብሮነት፣ ለስነ-ልቦና እድገትና ለሰብዓዊ ልማት ያለው ፋይዳም በጥናቱ እንደሚተነተን ነው ዶክተር አብዱራዛቅ ያብራሩት።
በዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ስነ-ፅሑፍና ቋንቋ ትምህርት ክፍል የፎክሎር መምህር ዶክተር መሃመድ አሊ፥ በመውሊድ በዓል የሚከወኑ ጥበባዊ ጉዳዮች (መንዙማ)፣ የተጣሉትን ማስታረቅ፣ የተቸገሩትን መርዳትና ሌሎች የመተሳሰብና የፍቅር እሴቶች የጥናት መነሻዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ገልጸዋል።
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ የበዓሉን የአካባበር ትውፊቶች ማጥናት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንደሚኖረው የገለጹት ደግሞ አምባሳደር ኡስታዝ ሃሰን ታጁ ናቸው።
የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ ዳይሬክተር ዶክተር ዮሐንስ አድገህ በበኩላቸው፥ በጥናቱ የመውሊድ በዓልን ትውፊታዊ ገጽታ በመቃኘት የሚገኘው እውቀትና ጥበብ ለአገርና ለህዝብ አንድነት የሚኖረው ፋይዳ እንደሚተነተን ገልጸዋል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸውንና ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል።