ቀጥታ፡

በሲዳማ ክልል ሕገወጥና ኮንትሮባንድ ንግድ መከላከል ሥራ ውጤት እየተገኘበት ነው

ሀዋሳ፤ታህሳስ 17/2016 (ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል በቅንጅት እየተተገበረ ያለው የሕገወጥና ኮንትሮባንድ ንግድ መከላከል ሥራ ውጤት እየተገኘበት እንደሆነ የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ በየነ በራሳ ተናገሩ፡፡

በሲዳማ ክልል ሕገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ መከላከልና የኑሮ ውድነት ማሻሻያ የጋራ ግብረ-ኃይል የባለፈው ዓመት የዕቅድ አፈፃፀምና የ2016 በጀት ዓመት ንቅናቄ ላይ የሚመክር መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የጋራ ግብረ-ኃይሉ ሰብሳቢ አቶ በየነ በራሳ "በክልሉ በተለይ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ሕገ ወጥ ንግድና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመከላከል በቅንጅት ተሰርቷል" ብለዋል።

ሕገ ወጥነትን ለመከላከልና ጤናማ የግብይት ሥርዓት ለመዘርጋት በተሰራ ሥራ ውጤት መገኘቱንም  ገልጸዋል።

ለአብነት የነዳጅ ግብይቱን ዘመናዊ በማድረግ በዘርፉ የሚስተዋሉ ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን በመቆጣጠር የማስተካከል ሥራ ማከናወን መቻሉን አስረድተዋል።

"ሕብረተሰቡ ላይ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉና መንግስትን ገቢ ሊያሳጡ የሚችሉ ያልተፈቀዱ ምግብ፣ መጠጦችና ሌሎች ቁሳቁሶችን በጋራ በመከታተልና በመቆጣጠር የተሻለ ሥራ ተሰርቷል" ብለዋል።

"የግብይት ሥርዓቱ ሕጋዊነትን ብቻ ያማከለ የማድረግ፣ የማዘመን እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የኑሮ ውድነት ጫና የመቀነስና የዜጎችን ሕይወት የማሻሻል ሥራዎች በልዩ ትኩረት የምንሰራባቸው ጉዳዮች ናቸው" ብለዋል።

የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሰላማዊት መኩሪያ እንደገለፁት በ2015 በጀት ዓመት ወደ ክልሉ ሲገቡ፣ ሲወጡና እየተጓጓዙ እያሉ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግምታቸው 138 ሚሊዮን 600 ሺህ ብር የሆነ የተለያዩ የኮንትሮ ባንድ ዕቃዎች ለመንግስት ገቢ እንዲሆኑ ተደርጓል።

በኮንትሮባንድ ሲዘዋወሩ ከተያዙ ምርቶች ውስጥ ቡና፣ ቤንዚል፣ አልባሳት እና የተለያዩ የፋብሪካ ምርቶች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ 64 ሺህ 125 የንግድ ተቋማት ላይ መደበኛና ድንገተኛ ፍተሻና ቁጥጥር መደረጉን ጠቅሰው ንግድ ፈቃድ ያልነበራቸው፣ ያለዘርፋቸው ሲነግዱ የነበሩ፣ ደረሰኝ የማይሰጡና ሌሎች ሕገ ወጥ ሥራን ሲሰሩ የነበሩ 24 ሺህ 125 ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን አስረድተዋል።

"በያዝነው በጀት ዓመት ባለፉት አምስት ወራት እንደ ክልል 8 ሺህ 972 በሕገ ወጥ ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላት ወደ ሕጋዊ የንግድ ሥርዓት ውስጥ እንዲገቡ አድርገናል" ብለዋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሽመልስ ቶማስ በበኩላቸው የኮንትሮባንድና ሕገ ወጥ ንግድ እንቅስቃሴ በኢኮኖሚው ላይ ከሚያሳድረው ጫና በተጨማሪ እንደ ሀገር በሰላምና ፀጥታ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

"ይህ ሕገወጥ እንቅስቃሴ ሊያስከትል በሚችለው አደጋ ልክ ዝግጅት በማድረግ በግብረ-ኃይሉ አማካይነት ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከጉምሩክ ኮሚሽን፣ ከክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮና ሌሎች አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው" ብለዋል።

ፖሊስ ኮሚሽኑ ተቋማዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አኳያ ሰፊ የፖሊስ ኃይል ስምሪት በመስጠት የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎችን በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ የደቡብ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ሱልጣን ኢሳ፣ ከክልሉ አስተዳደርና የፀጥታ አካላት፣ ከጉምሩክ ኮሚሽንና ሌሎች ባለድርሻዎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

"የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ከሀገር ኢኮኖሚና ፀጥታ ጋር ተያያዥነት ያለው ጉዳይ ነው'' ያሉት ኮማንደር ሱልጣን  ችግሩን ለመቅረፍም ቅንጅታዊ አሰራራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

በመድረኩ ላይ ከፌዴራልና ከሲዳማ ክልል እንዲሁም ከዞኖች ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም