ቀጥታ፡

ድንበር ተሻጋሪ ኢ-መደበኛ የቁም እንስሳትን ንግድ ለመቆጣጠር የባለድርሻ አካላት ሚና መጠናከር አለበት   

አዲስ አበባ፤ታህሣሥ 17/2016 (ኢዜአ)፦ድንበር ተሻጋሪ ኢ-መደበኛ የቁም እንስሳትን ንግድ ለመቆጣጠር የባለድርሻ አካላት ሚና መጠናከር እንዳለበት ተገለፀ። 

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የድንበር ተሻጋሪ ኢ-መደበኛ /ኮንትሮባንድ/ የቁም እንስሳት ንግድን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል። 

በመድረኩ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በግብርና ኢኮኖሚክስ ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ረሂማ ሙሰማ፤ ድንበር ተሻጋሪ ኢ-መደበኛ የቁም እንስሳት ንግድን በተመለከተ የጥናት ውጤት አቅርበዋል።

በዚህም ከድንበር ተሻጋሪ የቁም እንስሳት ንግድ ኢትዮጵያ ማግኘት በሚገባት ልክ ገቢ እያገኘች አይደለም ብለዋል። 

ለዚህም በርካታ ምክንያቶች የሚጠቀሱ ቢሆንም  በዘርፉ ያለ ኢ-መደበኛ ንግድ ዋነኛውን ሥፍራ እንደሚይዝም ተናግረዋል።   

ሕግና ደንብን ተከትሎ ወደ ውጭ ከሚላኩ የቁም እንስሳት በበለጠ በኢ-መደበኛ መልኩ የሚወጡት የበለጡ መሆኑን በጥናት መረጋገጡን ገልፀዋል።  

በዓመት ከ130 ሺህ በላይ የቁም እንስሳት በሕገ-ወጥ መንገድ በምስራቅ በኩል ወደ ውጭ እንደሚወጡ ጠቁመው፤ ይህም በሰሜን ምዕራብ፣ የምዕራቡን እና ደቡብን ሳይጨምር መሆኑንም ጠቁመዋል።   


 

የእንስሳት እርባታ የግጦሽ ልማት ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ሰለሞን ደስታ በዚሁ ጊዜ፤ ድንበር አከባቢ ያለውን የቁም እንስሳት ንግድ ወደ መደበኛው ሥርዓት እንዲገባ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለዚህም በአካባቢው በቂ የገበያ አገልግሎት መስጠትን ጨምሮ ከአጎራባች  አገራት ጋርም በመነጋገር የተቀናጀና የተናበበ ፖሊሲ ማውጣት እንደሚገባም ገልጸዋል። 


 

በኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪ ዶክተር ደሣለኝ ቤኛ እንዳሉትም፤ ሕገ-ወጥ የእንስሳት ንግድ በአገር ላይ በርካታ ችግሮች ያስከትላል ብለዋል። 

ሕገ-ወጥ የእንስሳት ንግድ አገሪቱ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ ከማሳጣት ባለፈ በአገር ውስጥ የቁም እንስሳት ዋጋ መናርን እንደሚያስከትልም ጠቁመዋል። 

ይህን ለመቆጣጠር መንግሥት የተለያየ ጥናቶችን ማድረጉን ጠቁመው፤ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተዘጋጀው የሕግ-ማዕቀፍ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩንም ጠቁመዋል። 


 

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የእንስሳትና እንስሳት ተዋጽዖ ወጪ ንግድ ግብይት ዴስክ ኃላፊ አቶ አበበ ታደሰ በበኩላቸው ኢ-መደበኛ የእንስሳት ንግድን ለመቆጣጠር ከጉሙሩክ ኮሚሽን ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

በዚህም በርካታ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚጓጓዙ እንስሳትን በመያዝ በአጓጓዦች ላይም ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ባሳለፍነው አምስት ወራት በህጋዊ መንገድ ከ84ሺህ በላይ የቁም እንስሳት ወደ ውጪ መላካቸውን ገልጸው ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ብልጫ ያለው መሆኑንም ጠቁመዋል።

ለዚህም በህገ-ወጥ መንገድ ሲወጡ የነበሩ እንስሳት ወደ ህጋዊ የንግድ ስርዓት መመለስ መቻላቸው እንደዋነኛው ምክንያት ይጠቀሳል ብለዋል። 

ኢትዮጵያ በቁም እንስሳት ሃብት በቁጥር ከአፍሪካ ቀዳሚ ስፍራ ላይ የምትገኝ ሲሆን ይህንን በመጠቀም ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ለማግኘት መሰራት እንዳለበትም ተጠቁሟል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም