ቀጥታ፡

አማራ ክልልን በኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ  ህጎችን የማሻሻል ስራ ይከናወናል -- እንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ 

ደብረብርሀን ፤ታህሳስ 17/ 2016 (ኢዜአ)፦ የአማራ  ክልልን በአምራች ኢንዱስትሪና ሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተመራጭ ለማድረግ ህጎችን እንደሚያሻሽል የክልሉ እንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው የኢንቨስትመንት ህጎችንና አሰራሮችን ለማዘመን የሚያስችል የውይይት መድረክ ከፍትህ አካላት ጋር በደብረ ብርሃን አካሂዷል።

የክልሉ እንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ክልሉ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በማዕድንና ሌሎች ዘርፎች እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም አለው።

በዚህም ባለፉት አምስት ወራት ብቻ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለ94 ፕሮጀክቶች የግንባታ ቦታ መስጠት እንደተቻለ ገልጸዋል።

በቅርቡም ጥያቄ ካቀረቡ ባለሃብቶች ውስጥ በክልሉ የኢንቨስትመንት ቦርድ አዋጭ መሆናቸው ለተረጋገጡ  86 ፕሮጀክቶች ወደ ስራ እንዲገቡ መወሰኑን አውስተዋል።

ፍቃድ እንዲሰጥ የተወሰነውም በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት ዘርፍ ለባለ አራትና አምስት ኮከብ ሆቴሎች፣ ሎጅዎችና ሌሎች የከተማ ኢንቨስትመንት ዘርፎች መሆኑን አስገንዝበዋል። 

የዛሬው መድረክም ባለሃብቶችን በማስተናገድ በኩል በኢንቨስትመንት ህጉና አሰራሩ ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ከህግ አካላት ጋር ተባብሮ በመፍታት የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት ያለመ ነው ብለዋል። 

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በበኩላቸው የደብረ ብርሃን ከተማን የኢንዱስትሪ፣ የቱሪዝምና የንግድ መዳረሻ  ለማድረግ እየተሰራ ነው።  

ለከተማዋ ኢንቨስትመንት መጨመርም "የኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ  ለውጥ ማስገኘቱን የገለጹት አቶ በድሉ በዚህ ዓመት ሰባት ፕሮጀክቶች በተደረገላቸው ድጋፍ ወደ ማምረት መሸጋገራቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ሌሎች 17 ፕሮጀክቶች በቅርቡ ወደ ማምረት እንደሚሸጋገሩ ጠቁመው ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ለ36 ፕሮጀክቶች መሬት መሰጠቱን ተናግረዋል። 

የክልሉ ፍትህ ቢሮ ሃላፊ አቶ ብርሃኑ ጎሽም በበኩላቸው መሬትን ከ3ኛ ወገን በማጽዳት ለባለሃብቱ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር፣ በመሬትና ሃብት ግመታና ሌሎች ጉዳዮች ለሚመጣ ክስ አፋጣኝ ፍትህ መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በተጨማሪም በየጊዜው የሚነሱ ውዝግቦችን ለማስቀረት የንቃተ ህግ የማስተማር ስርአት በመዘርጋት የህብረተሰቡን የግንዛቤ ደረጃ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ አስረድተዋል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አብየ ካሳሁን እንደገለጹት የደብረ ብርሃን ከተማ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በክልሉም ሆነ በአገር ደረጃ ፈጣን እምርታ የታየበት ነው።

ፍርድ ቤቱ በኢንቨስትመንት ህግ፣ መመሪያና ደንብ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችንና ማነቆ የሆኑ ጉዳዮችን በጋራ ለይቶ ለመፍታት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በውይይት መድረኩ ላይም ከቢሮው በተጨማሪ ከፍትህ፣ ፍርድ ቤት፣ ፖሊስና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ አመራሮችና ባለሙያዎች መሳተፋቸው ታውቋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም