በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እጅን አዘውትሮ በውሃና በሳሙና የመታጠብ ልምድን በማዳበር ተላላፊ በሽታዎችን የመከላከል ንቅናቄ ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እጅን አዘውትሮ በውሃና በሳሙና የመታጠብ ልምድን በማዳበር ተላላፊ በሽታዎችን የመከላከል ንቅናቄ ተካሄደ

ጂንካ፤ ታህሳስ 17 /2016 (ኢዜአ) ፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እጅን አዘውትሮ በውሃና በሳሙና የመታጠብ ልምድን በማዳበር ተላላፊ በሽታዎችን የመከላከል ጥረቶች የሚያግዝ ንቅናቄ መካሄዱን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ።
"ከታጠበ እጃችን ይጠበቃል ጤናችን'' በሚል መሪ ሀሳብ የዓለም አቀፍ የእጅ መታጠብ ቀን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአሪ ዞን ጂንካ ከተማ በኔሪ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከብሯል።
በዚህን ጊዜ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል አቶ መና መኩሪያ፥ እጅን አዘውትሮ በውሃና በሳሙና የመታጠብ ልምድ በማዳበር ተላላፊ በሽታዎችን መከላከል እንደሚቻል አስታውሰዋል።
ጥናቶችን በመጥቀስ 80 በመቶ የሚሆኑት በሽታ አምጪ ተዋሲያን ወይም ጀርሞች የሚተላለፉት በእጅ አማካኝነት ነው ብለዋል።
በክልሉ እነዚህንም በሽታዎች ለመከላከል ዘወትር እጅን በውሃና በሳሙና የመታጠብ ልምድን በማዳበር ተላላፊ በሽታዎችን እና የአንጀት ጥገኛ ተዋህስያን መከላከል የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ዓለም አቀፍ የእጅ መታጠብ ቀን በየዓመቱ ከጥቅምት ወር መጨረሻ እስከ ታህሳስ ወር መባቻ የተለያዩ የግንዛቤ መስጫ ትምህርቶችን በመስጠት እንደሚከበር ተናግረዋል።
በጤና ዘርፍ የታቀደውን ዘላቂ የጤና የልማት ግብ ለማሳካት በበሽታ መከላከሉ ረገድ አሳታፊ በሆነ መልኩ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
ይህን ለማሳካት በተለይም የግልና የአከባቢ ንፅህና መጠበቅ ባህል ሆኖ መቀጠል አለበት ያሉት አቶ መና፥ ለዚህም በትምህርት ቤቶች፣ በቤተሰብ ደረጃ እንዲሁም በገጠር አካባቢዎች እየተሰጠ ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በተጠናከረ ሁኔታ ይቀጥላል ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጂንካ ቅርንጫፍ ተወካይ ወይዘሮ ባህረወሰን ወልደአረጋይ፥ ማህበሩ ከሰብአዊ ድጋፎች ባሻገር በግልና በአካባቢ ንፅህና አጠባበቅ ላይ በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም ማህበሩ ይህንን ተግባር በማጠናከር በግልና በአከባቢ ንፅህና አጠባበቅ ምክንያት የሚመጡ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል ከጤና ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
በአካባቢው የአይን ጤና ላይ እየሰራ የሚገኘው 'ኦርቪስ ኢንተርናሽናል' ተወካይ አቶ ማሌ ማቴ በበኩላቸው ድርጅቱ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በአይን ጤና አጠባበቅ ረገድ ከጤና ተቋማት ጋር በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን ገልፀዋል።
ከአይን ጤና እክል መንስኤዎች አንዱ ትራኮማ እንደሆነ ገልፀው ትራኮማን ለመከላከል የግልና የአከባቢ ንፅህናን መጠበቅ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የጅንካ ኔሪ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ5ኛ ክፍል ተማሪ ነፃነት ሽመልስ፥ የዘንድሮው የአለም እጅ መታጠብ ቀን በትምህርት ቤቱ መከበሩ ተማሪዎች ዘወትር እጅን በውሃና ሳሙና የመታጠብ ልምድን እንዲያዳብሩ ያበረታታል ብለዋል።
ከዚህ ቀደምም በትምህርት ቤቱ ባለው የንጽህና ክበብ አማካኝነት በግልና በአከባቢ ንፅህና አጠባበቅ ዙሪያ የሚሰጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን የሚያጠናክር መሆኑን ገልጻለች።
የአለም እጅ የመታጠብ ቀን መርሃ ግብር የክልል፣ የዞንና የጂንካ ከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች፣ አጋር ድርጅቶች ተወካዮች፣ የኔሪ መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን እና ተማሪዎች ተሳትፈዋል።