ቀጥታ፡

በአጎራባች አርብቶ አደሮች በውሃ ሰበብ የሚነሱ ግጭቶችን ያስወገደው 'የቡሪ አርባ' የወዳጅነት ኩሬ ለአካባቢው ነዋሪዎች ትልቅ እፎይታ ሰጥቷል

ጭሮ፤ ታህሳስ17/2016(ኢዜአ) ፡-በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በአጎራባች አርብቶ አደሮች በውሃ ሰበብ የሚነሱ ግጭቶችን ያስወገደው 'የቡሪ አርባ' የወዳጅነት ኩሬ  ትልቅ እፎይታ ሰጥቶናል ሲሉ አርብቶ አደሮች ይናገራሉ።

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ጉምቢ ቦርደዴ ወረዳ የ'ቡሪ አርባ' አርብቶ አደሮች መንደር ''በውሃ ማቆሪያ ግድቦችና ኩሬ ፕሮጀክቶች ግንባታ ህይወታችን በእጅጉ ተቀይሯል፣ አዲስ ቀን ነው የመጣልን'' ሲሉም ይገልጻሉ፡፡


 

ኢዜአ ያነጋጋራቸው አርብቶ አደሮች በቡሪ አርባ ኩሬ የታቆረው ውሃ ከከብቶች መጠጥ ባለፈ የጓሮ አትክልቶችን በማልማት አርብቶ አደሩ ወደ ከፊል አርብቶ አደርነት እየተለወጠበት ነው፡፡ 

የአካባቢው አርብቶ አደሮች እንደሚሉት፤ የጉምቢ ቦርዶዴ ወረዳና የአጎራባች አካባቢዎች አርብቶ አደሮች ለከብቶቻቸው ውሃ ፍለጋ ብዙ ይሰቃዩ ነበር፣ አሁን በኩሬው የታቆረው ውሃ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን እያቃለላቸው መጥቷል።

የቡሪ አርባ አካባቢ ማህበረሰብ የከብቶች መጠጥ ውሃ ፍለጋ አዋሽን ተሻግሮ ከዱር እንስሳት ጋር እየታገለ ውሃ ጥምና ረሃብ እየተፈራረቀበት በርካታ ኪሎ ሜትሮችን ሲጓዝ ኖሯል።

በዚህም በአካባቢው አርብቶ አደሮች መካከል ውሃን መነሻ ያደረገ ግጭት እየተከሰተ ብዙ ችግሮች ያጋጥም ነበር።  

በወዳጅነት የተሰየመው የቡሪ አርባ የውሃ ኩሬ ከተገነባ በኋላ ከአጎራባች አካባቢዎች የሚመጡ አርብቶ አደሮች ከብቶቻቸውን በጋራ ውሃ እንደሚያጠጡና ያለምንም ግጭት መኖር ያስቻላቸው የሰላም ኩሬ እንደተገነባላቸው ይናገራሉ፡፡

ከአካባቢው አርብቶ አደሮች መካከል አሊ ኢብሮ በበረሃማው አካባቢያቸው የነበረው የከብቶች መጠጥ ውሃ ችግር በኩሬው መፈታቱን ይናገራሉ።


 

ለብዙ ዓመታት የከብቶች መጠጥ ውሃ ፍለጋ ብዙ ርቀት በመጓዝ ከጤና ችግሮች አልፎም ለግጭትና ከባድ አደጋ ሲጋለጡ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል ፡፡

የውሃ ኩሬው በቡሪ አርባ ላይ ከተገነባላቸው በኋላ በምቹ ሁኔታ ያለምንም እንግልት ከብቶቻቸውን ንጹህ ውሃ አጠጥተው ወደ ተቀረው ስራቸው በመመለስ ጊዜያቸውንም መቆጠብ መቻላቸውን አንስተዋል። 

ሌላው የወዳጅነት ተምሳሌት ሆኖ ሰላምና መረጋጋትን በአካባቢው  ስላሰፈነው የቡሪ አርባ የውሃ ማቆሪያ ኩሬ የተናገሩት አርብቶ አደር በክሪ መሐመድ ፤ ቀደም ባለው ወቅት ያጋጥሟቸው የነበሩ ብዙ ችግሮችን አልፈው በቅርባቸው በተገነባላቸው ኩሬ ከብቶቻቸውን አጠጥተው በሰላም ተሰማርተው ወደ ቤታቸው እንደሚገቡ አንስተዋል፡፡

የክልሉ መንግስት  'ፊነ' በተሰኝ የአርብቶ አደሩን የውሃ ችግር ለመፍታት በተቀረጸ ፕሮጀክት አማካኝነት "የአርብቶ አደሩን ችግር በጥልቀት ተገንዝቦ ለሰራው ስራ ትልቅ ምስጋና ይገባዋል" ብለዋል፡፡

''እኛም ከብቶቻችንም ውሃ ፍለጋ በበረሃ በመጓዝ ለጤና ችግርና ለአደጋ ጭምር ስንጋለጥ በርካታ በጋና ክረምቶች አሳልፈናልም'' ብለዋል።

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ጉምቢ ቦርደዴ ወረዳ የመስኖና አርብቶ አደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሁሴን ፈንታሌ እንደሚሉት፤ የቡሪ አርባ የውሃ ኩሬ የውሃ ችግርን ብቻ ሳይሆን የሰላም መደፍረስ ችግርንም የፈታ ነው፡፡

አርብቶ አደሩም በአንድ አካባቢ ቋሚ ህይወት መመስረት እንዲችልና የተረጋጋ ኑሮ በመኖርና በመስኖ በመታገዝ "ወደ ከፊል አርብቶ አደርነት የተለወጠበት ነው" ብለዋል፡፡

የቡሪ አርባ የውሃ ኩሬ ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ ውሃ መያዝ የሚችል ኩሬ መሆኑንና ለአካባቢው አርብቶ አደሮች ችግር መፍትሄ የሰጠ መሆኑን ነው የገለጹት።


 

እንደ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሁሴን ገለጻ፤ በወረዳው ከ761 ሺህ በላይ የቀንድ ከብቶች ይገኛሉ። ከከብቶች ባልተናነሰ ደረጃ ግመል በማርባት የሚታወቅ ወረዳ ነው፡፡ 

አርብቶ አደሩ በከብት እርባታ ብቻ እንዳይወሰንና መስኖን በመጠቀም በሰብል ምርቶች እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ውጤታማ እንዲሆንም በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል፡፡

  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም