ቀጥታ፡

የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ንግስ በዓል በሰላም እንዲከበር ዝግጅት ተደርጓል - አቶ መኩሪያ ማርሻዬ

ሀዋሳ ፤ ታህሳስ 17/2016 (ኢዜአ) ፦ የፊታችን ታህሳስ 19 የሚከበረው የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ንግስ በዓል  በሰላም እንዲከበር ዝግጅት መደረጉን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ መኩሪያ ማርሻዬ አስታወቁ።

የሀዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ መኩሪያ ማርሻዬ በዓሉን አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

አቶ መኩሪያ በመግለጫቸው እንደተናገሩት በከተማዋ ታህሳስና ሐምሌ 19 የሚከበረው ዓመታዊ ቅዱስ ገብርኤል የንግስ በዓል በርካታ ምዕመናንና ጎብኝዎች የሚታደሙበት ነው።

በበዓሉ ላይ ለመታደም የሚመጡ ምዕመናንና ሌሎች እግዶችን በአግባቡ ተቀብሎ ማስተናገድ የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

ለበዓሉ የሚመጡ እንግዶች በከተማዋ በሚኖራቸው ቆይታ ደህንነትና ምቾት ተሰምቷቸው እንዲያሳልፉ በሰላምና ጸጥታ ማስከበር ዘርፍ የተለያዩ ተግባራት ከወዲሁ መጠናቀቃቸውን አመልክተዋል።

ከተማ አስተዳደሩ በየደረጃው ካሉ የከተማዋ ማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ሰፊ ውይይት በማድረግ ከወዲሁ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

ከተማዋ ለ24 ሰዓት በደህንነት ከሜራ ጥበቃ ሥር መሆኗን አስታውሰው ልዩ ጥበቃ በሚያስፈልጋቸው ቦታዎች የፀጥታ ኃይሎችን ከወጣቶችና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በማቀናጀት የሰው ኃይል የመመደብ ሥራ መሰራቱን አስረድተዋል።

ምክትል ከንቲባው አክለውም ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጡ ምዕመናንና ሌሎች ጎብኝዎች በከተማዋ በሚኖራቸው ቆይታ ለሚያገኙት አገልግሎት ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግባቸው የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱንም ገልጸዋል።

በተለይ ሆቴሎችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በቅናሽ ዋጋ አገልግሎት እንዲሰጡና ወግና ባህልን በአግባቡ በማስተዋወቅ የእንግዶችን ቆይታ የሚያራዝሙ እንዲሆኑ ከመግባባት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል።

ከተማችን ሀዋሳ በሠላም፣ በአብሮነትና በመቻቻል ትልቅ እሴት የገነባች ትንሿ የኢትዮጵያ ተምሳሌት የሆነች ከተማ ናት ያሉት ምክትል ከንቲባው ይህ እሴቷና ሠላማዊነቷ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

ከተማዋ በርካታ ሀገር አቀፍና ክልላዊ ኩነቶች እንዲሁም ህዝባዊና ሐይማኖታዊ ኩነቶች በተሳካ ሁኔታ የሚከናወኑባት እንደሆነችም ጠቅሰዋል።

ለዚህ ደግሞ የፀጥታ መዋቅሩ ከሚያከናውናቸው መደበኛ ተግባራት ባለፈ በየደረጃው ያለው የከተማዋ ማህበረሰብ ራሱን የሠላም ባለቤት አድርጎ በመስራቱ እንደሆነ ተናግረዋል።

በአሁን ወቅት ከተማዋ ከሀገር ውስጥ ሆነ ከውጭ የሚመጡ እንግዶችን ተቀብላ ያለ ምንም የፀጥታ ችግር ለማስተናገድ ሙሉ ዝግጅት ማድረጓን ገልፀው የዕምነቱ ተከታዮችና ሌሎች ጎብኝዎች ያለ ሥጋት በዓሉን ለመታደም እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም