ቀጥታ፡

ሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ ጥሪን የተሳካ ለማድረግ የተቋቋመው ዐቢይ ኮሚቴ የዝግጅት ስራዎችን አጠናቋል - አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 17/2016(ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ የተቋቋመው ዐቢይ ኮሚቴ የዝግጅት ስራዎችን ማጠናቀቁን የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ገለጹ።

ጥሪውን ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት ለሚመጡ ዳያስፖራዎች የተለያዩ ሁነቶች መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል።

አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ የሁለተኛው ትውልድ የዳያስፖራ ጥሪን አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተከትሎ በቱሪዝም ሚኒስቴር የሚመራና የተለያዩ ባለድርሻ ተቋማትን ያቀፈ ዐቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሰፊ ዝግጅት ሲከናወን መቆየቱን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

ኮሚቴው የዳያስፖራ አባላቱ ከታህሳስ 20 ቀን 2016 እስከ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም በሶስት ዙር ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ ለማስቻል እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ብዝሃ ባህል ያላትን ኢትዮጵያን ለመጪዎቹ የዳያስፖራ አባላት በይበልጥ ለማስተዋወቅ "የኢትዮጵያ ሳምንት" በሚል የተዘጋጀ የባህል የኪነ-ጥበብና ሌሎች ዐቢይ ኩነቶች እንደሚኖሩም ነው የጠቆሙት።

የመጀመሪያ ዙር ከታህሳስ 20 እስከ ጥር 20/2016 ድረስ እንደሚቆይና 'connect to your multi culture' በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚከናወን ጠቅሰዋል።

ሁለተኛው ዙር ደግሞ 'connect to your history' በሚል መሪ ሀሳብ በየካቲት ወር 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሚካሄደው የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ እንደሚካሄድ ነው ሚኒስትሯ ያብራሩት።

ሶስተኛው ዙር 'live your legacy' በሚል ከ2016 ዓ.ም የክረምት መግቢያ ጀምሮ እስከ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

በሁለተኛው ዙር የአድዋ የድል በዓልና ታሪካዊ ክዋኔዎችን ለሁለተኛው ትውልድ ገለጻ የሚደረግበት ሁነትን ጨምሮ የጉዞ መርሐ ግብሮች እንደሚኖሩ ገልጸዋል።

ጥሪው በውጭ ሀገራት የተወለዱ ሁለተኛ ትውልድ የዳያስፖራ አባላት ባህላቸውን ይበልጥ እንዲያውቁ ለማስቻልና ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ትስስር የማጠናከር ዓላማ አለው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በውጭ ሀገራት ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰሩ መሆኑንም ሚኒስትሯ አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም