ቀጥታ፡

አቶ አህመድ ሺዴ ከአዲሱ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሀፊ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ታህሣሥ 17/2016(ኢዜአ)፦የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ አዲሱን የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሀፊን ሚስተር ክላቨር ጋቴቴን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይታቸውም ኢትዮጵያና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ግንኙነታቸውን አጠናክረው አብረው በሚሰሩበት ሁኔታ መክረዋል።

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሀፊውን የአፍሪካ ህብረት መዲናና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መቀመጫ ወደ ሆነችው አዲስ አበባ እንኳን በደህና መጡ በማለት የተቀበሏቸው አቶ አህመድ ኢትዮጵያና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የአፍሪካውያን የጋራ ድምጽ በአለም መድረክ እንዲሰማ በጋራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ እድገትና ልማቷን ለማፋጠን የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳን ጨምሮ የተለያዩ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን እየወሰደች መሆኑንም አመልክተዋል።

በምስራቅ አፍሪካና በአፍሪካ አህጉር ደረጃ የኢኮኖሚ ልማትን ለማምጣትና ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጋር በቅርበትና በትብብር እንደምትሰራም ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡

በወቅቱ የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሺየቲቭ ሊቀመንበርነታቸውም በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት መካከል ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለማጎልበት በሚያደርጉት ጥረት ከአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በተጨማሪ በርካታ አለም አቀፍ ተቋማትንና ሀገራትን በአባልነት ያቀፈው ኢኒሺየቲቭ ውጤታማ እንዲሆን ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጋር በጥምረት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም ጨምረው አስረድተዋል፡፡

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሀፊ ሚስተር ክላቨር ጋቴቴ በበኩላቸው ስለኢትዮጵያ ብዙ ማወቅ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የተቋቋመው ለአፍሪካውያን በመሆኑ አፍሪካውያን በአለም መድረክ የጋራ ድምጻቸው እንዲሰማ ኮሚሽኑና የአፍሪካ የፋይናንስ ሚኒስትሮች በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል ማለታቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የአፍሪካ የፋይናንስ፣ የፕላንና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሮች 56ኛው ጉባኤ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዘጋጅነት በመጋቢት 2016 ዓ.ም በዚምቧቤ የሚካሄድ መሆኑን በውይይቱ ወቅት የተገለጸ ሲሆን ጉባኤውም ወደ አሳታፊና አረንጓዴ ኢኮኖሚ የሚደረገው ጥረት በገንዘብ የሚደገፍበት ሂደት ላይ እንደሚመክር ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም