የወልቂጤ ከተማ ሆቴልና ቱሪዝም እንቅስቃሴ መነቃቃት ተፈጥሯል 

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 17/2016 (ኢዜአ)፦ የወልቂጤ ከተማ በሆቴልና ቱሪዝም እንቅስቃሴ መነቃቃት መፈጠሩን በሆቴል ዘርፍ የተሰማሩ ባለኃብቶች ገለጹ። 

ከአዲስ አበባ 160 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ወልቂጤ ከተማ የእድሜዋን ያህል ዕድገት ባታሳይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሁለንተናዊ እምርታ ላይ መሆኗን ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል።


 

ለረጅም ዘመን በሆቴል አገልግሎት የተሰማሩት አቶ ሠይፉ ኃይለማርያም ወልቂጤ ለአዲስ አበባ ቅርበቷ፣ የበርካታ ከተሞች መተላለፊያና የመንገደኞች ማረፊያነቷና በዙሪያዋ የቱሪስት መዳረሻ ጸጋዎች መኖራቸው ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ከተማ እንደሚያደርጋት ይናገራሉ።

አሁን ደግሞ በአዲስ የተደራጀው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት መቀመጫ መሆኗ በሆቴልና ንግድ ለተሰማራው ሕዝብ ትልቅ ዕድልና ተስፋ ይዞ በመምጣቱ ከተማዋ በመነቃቃት ላይ እንደሆነች ገልጸዋል።

እሳቸውም በሆቴል አንቨስትመንት ማስፋፊያ በቅርብ ጊዜ እንደሚያጠናቅቁ ገልፀው፤ ሰፋፊ ስብሰባ አዳራሾች፣ የባህል ቤቶች፣ ልዩ ማረፊያ ክፍሎችን ጨምሮ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጥ ዝግጁ መደረጉን ገልጸዋል።

በዘርፉ ባለኃብቶችም በሆቴልና ቱሪዝም ላይ እንቨስትመንት እየተሳተፉ በመሆኑ በቀጣይ ወልቂጤ ከተማ የኮንፈረስ ቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን የሚያስችል እንቅሰቃሴ መኖሩን ገልጸዋል።

ወልቂጤና አካባቢው በመንገድ መሰረተ ልማት ያለበትና ለማዕከላዊ ገበያ ያለው ቅርበት ለኢንቨስትመንት ተመራጭ በመሆኑ ባለኃብቶች በአምራችና አገልግሎት ዘርፍ ቢሰማሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።

ሰላም ማረጋገጥና የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችን ማሻሻል ለኢንቨስትመንት ፍሰት ካለው ፋይዳ አኳያ በመንግሥት ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራበትም ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል የወልቂጤ ከተማ መሰረታዊ ችግር ሆኖ የቆየው የውኃ አቅርቦት ማሻሻል ቢያሳይም አሁንም ሰፊ ሥራ እንደሚጠይቅ ገልጸው፤ መንግሥት ለችግሩ ዘላቂ መፈትሄ እንዲሰጠው ጠይቀዋል።


 

ከሁለት ወራት በፊት የባለሶስት ኮኮብ ደረጃ ያለው ሆቴል ወደ አገልግሎት ያስገቡት አቶ ዮናስ ሙሉ በበኩላቸው የክልል ምክር ቤት መቀመጫ መሆኗ ለቱሪስት መዳረሻነቷ  ተጨማሪ አቅም ነው ይላሉ።

እንደ ዘርፉ ተዋናይ ሆቴላቸው የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲጎለብት የሚበጁ ዝግጅቶች ማድረጋቸውን ነው የተናገሩት። 

በሌላ በኩል ባለ ሦስት ኮከብ ሆቴል ኢንቨስመንት ፈቃድ ወስደው ግንባታ ሥራ ከጀመሩት ፕሮጀክቶች መካከል የጋሽ ኃይሌ ሆቴል ድርጅት ሥራ እስኪያጅ አቶ ደግፌ ዋቄ፣ በመንግሥትና በሕዝቡ ዘንድ ለአልሚ ለባለኃብት እየተደረገ ያለው ትብብር የሚበረታታ እንደሆነ ገልጸዋል።


 

ወልቂጤ ከተማ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በፈጣን እንቅስቃሴ ላይ መሆኗንና የአካባቢው ተወላጆችም ወደ ኢንቨስትመንት እየገቡ መሆኑን ጠቁመው፣ መንግሥት ምቹ መሰረተ ልማት ማሟላት ላይ ሥራው እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

የከተማዋ ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው፤ የከተማ አስተዳድሩ አዲስ አመራር ከተማዋን ለማዘመን ዕድልና ተግዳሮች ለይቶ ህዝቡንና ባለሀብቱን ያሳተፈ ልማት ለማረጋገጥ እቅድ ይዞ እየሰራ ነው።


 

ከተማዋን አማራጭ የኮንፈረንስ ማዕከል ለማድረግና ኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ያሏቸውን አልሚዎች ወደ ሥራ ለማስገባት ፈጣን አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

ቀደም ብሎ በተለያዩ የማምረቻና አገልግሎት ዘርፎች ጥያቄ ቀርበው ግን ወደ ተግባር ያልተለወጡ ወደ 300 ሚሊየን ብር ካፒታል ያላቸው 23 ፕሮጀቶችን እንደነበሩ ገልጸዋል።

በዚህም ኢንቨስመንት ፕሮጀክቶች መርምሮ በአጭር ቀናት ውስጥ ቢያንስ 10 ፕሮጀክቶች ወደስራ እንዲገቡ መሬቱን የማስረከብና ተያያዥ ስራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በከተማዋ ግንባታቸው ያልተጠናቀቁ ሆቴሎችን አጠናቆ ወደ አገልግሎት በማስገባት የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር እና ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ በትኩረት መሰራቱን ገልጸዋል።

ከተማዋ አሁን ላይ ማንኛውንም ኮንፈረስ ለማስተናገድ የሚችሉ ሆቴሎች ወደ ሥራ መግባታቸውን ነው የጠቆሙት።

ከተማ አስተዳደሩ ሌሎች ባለኃብቶች መጥተው እንዲያለሙ ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ቁርጠኛ በመሆኑ ፍላጎት ያላቸው ግለሰበች በከተማዋ ፈቃድ ወስደው እንዲያለሙ ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል የወልቂጤ ከተማ ተግዳሮት የነበረውን ከውሃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የ300 ሚሊዮን ብር ፐሮጀክት ዕውን ለማድረግ ረቂቅ ፕሮጀክቱ ለሚመለከተው አካል መቅረቡን ጠቁመዋል።

ለወቅታዊ የውሃ አቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍ ግን መዋቅሩን የማሻሻልና የጥገና ባለሙያዎችን በመጨመር በህገ ወጥ መንገድ የተቀጠሉ መስመሮችን ማስተካከል፣ የውሃ መጠንና ስርጭትን ማሻሻል ስራዎች እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ከፌዴራል መንግስት 26 ነጥብ 8 ሚሊየን የሚገመቱ የውሃ አገልግሎት ማሻሻያ መሳሪያዎችን ድጋፍ በመቀበልም መስመሮችን የማሻሻል፣ ምንጮችን አቅም ማጎልበት ስራዎች በማከናወን ትልቅ ለውጥ መምጣቱን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም