ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ለዓመታት ደብዛው የጠፋውና አሁን ላይ እያንሰራራ ያለው የኳየር ሙዚቃ 

አዲስ አበባ፤ ታህሣስ 17/2016 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ለዓመታት ደብዛው የጠፋውና አሁን ላይ እያንሰራራ ያለው የኳየር ሙዚቃ 

የኳየር ሙዚቃ ቢያንስ  ሁለትና ከዛ በላይ በሆኑ ድምፆች የሚሰራ የተለያዩ ሙዚቀኞች ከሙዚቃ መሣሪያ ጋር ወይም በድምፅ ብቻ የሚሳተፉበት  የሙዚቃ ዘውግ ነው።

የኳየር ሙዚቃ መነሻ ባህላዊ ሙዚቃዎች ሲሆኑ ለዚህም ማሳያ በጥንታዊቷ ግሪክ፤ በኋላም በአውሮፓ ውስጥ በጋራ ባህላዊ ሙዚቃዎችን በተለያየ ሕብረ ድምፅ የሚጫወቱ ሰዎች ማሳያ ናቸው። 

ምዕራባዊ ቅርፅ ያለው የኳየር ሙዚቃ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በ17ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ በመጡ ሚሲዮናውያን ሲሆን በከፍተኛ ደረጃ የተስፋፋው ደግሞ፤ በአርመኖች አማካኝነት ነው።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1924 ዓ.ም ኢትዮጵያ የደረሱት አርመናዊው ኬቮርክ ናልባንዲያን፤ 40 አርመናውያን ታዳጊ ልጆችን ይዘው የሰሩት የኳየር ዝማሬ በቀዳሚነት ይጠቀሳል።

በኋላም ሙሴ ነርሲስ ናልባንዲያን የኢትዮጵያን ተወዳጅ ሙዚቃዎች ወደ ኳየር ሙዚቃ የቀየሩበትና፤ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህር የነበሩት ዮናስ አያና በሰፊው ኳየርን ያስተማሩበት በዋነኝነት ይነሳል።

ይሁንና የሙዚቃ ዘውጉ ለበርካታ ዓመታት ተዳፍኖ የቆየ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኳየር ሙዚቃ የሚጫወቱ ባለሙያዎች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። 

ከእነዚሀ ሙዚቀኞች መካከል "መረዋ" እና "መራኪ" የኳየር ቡድንን በማቋቋም እየሰራ የሚገኘው  ምዕራፍ ተክሌ ተጠቃሽ ነው። 


 

በኢትዮጵያ ለኳየር ሙዚቃው መዳከም የተለያዩ ምክንያቶች የጠቀሰው ሙዚቀኛው የኳየር ሙዚቃ እንዲያድግ በትኩረት መሥራት ይገባል ብሏል። 

የኳየር ሙዚቃ፤ በኢትዮጵያ ሀገር በቀል ባህል ውስጥ እንደሚገኝ ጠቅሶ፤ የሙዚቃ ዘውጉ ትኩረት ቢሰጠው የጥራት ችግር የሚነሳበት የኢትዮጵያ ሙዚቃን፤ በአፍሪካና በዓለም ደረጃ ከፍ ለማድረግ እንደሚረዳ ተናግሯል።

ከሙዚቃ ዕድገት ባሻገር የኢኮኖሚ መስህብ ለመፍጠርና የሀገር ገፅታን ለመገንባት ስለሚረዳ ትኩረት ተሰቶበት ቢሰራ፤ ሀገሪቱ ውጤታማ እንደምትሆንበት ገልጿል።

በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ በኳየር ሙዚቃ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱት የሙሴ ነርሲስ ናልባንዲያን ልጅ፤ ሙዚቀኛ ቫርተስ ነርሲስ ናልባንዲያን በበኩላቸው፤ የኳየር ሙዚቃ የኅብረተሰቡን ሙዚቃ እይታ እንደሚያዳበር ይናገራሉ።


 

አንድ ሰው በስቱዲዮ ብቻ ተወስኖ የሚሰራው ሙዚቃ፤ የኢትዮጵያን የሙዚቃ ባህሪ ስለሚያዛበው የተለያዩ መሣሪዎችንና ሰዎችን በማሳተፍ፤ ኳየር መሥራት የኢትዮጵያን ሙዚቃ ያሳድጋል ብለዋል።

እንደ ቴአትር ቤቶች ያሉትን ቦታዎች ደግሞ፤ የኳየር ሙዚቃ ልምምድ እንዲደረግባቸው ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የሙዚቃ ባለሙያ ሠርፀ ፍሬ ስብሐት፤ የኳየር ሙዚቃ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ እድገትና ብሔራዊ ስሜትን የሚፈጥሩ ሙዚቃዎችን ለትውልድ ለማስተላለፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ይገልፃል።


 

የኳየር ሙዚቃ ሀገር በቀል በሆነው የኢትዮጵያ ባህል ውስጥ ስለሚገኝ፤ የምዕራባውያን ሙዚቃ ብቻ ነው ተብሎ ችላ ሊባል እንደማይገባው ያሳስባል።

አገራዊ ሥራዎች በኳየር መልክ ተቀናብረው ወደ ሕዝብ እንዲደርሱ ለማድረግ ቢሮው እንደሚሰራ ገልጿል።

ኳየርን ለማሳደግ በግለሰብ ብቻ ጥረት ስለማይቻልና ተቋማዊ መልክ መያዝ ስላለበትም፤ ሙዚቀኖችን በመደገፍና በማገዝ የኳየር ሙዚቃ እንዲሰሩና እንዲቀርፁ ሁኔታዎች እንደሚመቻቹ ተናግሯል።

ዓለም አቀፉ የኳየር ቀን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከታህሣሥ 10 ቀን ጀምሮ እስከ አውሮፓውያኑ ዘመን መለወጫ በዓል ቀን ድረስ፤ የተለያዩ የኳየር የሙዚቃ ቡድኖች በሚያቀርቡት ሕብረ ዝማሬ ይከበራል።

በሀገራችንም ታህሣሥ 12 ቀን 2016 ዓ.ም በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት "1ኛው የኳየር ሕብረ ዝማሬ ቀን አከባበር በኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሀሳብ፤ በሙዚቃ ባለሙያ ምዕራፍ ተክሌና በአቋቋመው "መራኪ" የኳየር ሙዚቃ ቡድን አማካኝነት የሙዚቃ ባለሙያዎች በተገኙበት መከበሩ ይታወሳል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም