ቀጥታ፡

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  የዲፕሎማሲ ስራ ላይ  ተሳትፎአችንን እናጠናክራለን -የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሁራን

ቦንጋ ፤ ታህሣስ 17/2016 (ኢዜአ)፡-በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  የዲፕሎማሲ ስራ ላይ  ተሳትፎአቸውን እንደሚያጠናክሩ   የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሁራን ገለጹ።

ኢትዮጵያ ሌሎች የአባይ ተፋሰስ አገራትን በማይጎዳ አካሄድ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ግንባታ ጀምራ በብዙ ጫናዎች ውስጥ እያለፈች ስኬታማ በመሆን ላይ ትገኛለች። 

በግድቡ ዙሪያ ምሁራን ሊኖራቸው የሚገባው ሚናና በተመለከተ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ሀሳባቸውን ለኢዜአ ሰጥተዋል።

ግድቡ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የምርምር ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶክተር ገዛኸኝ ደገፌ አወስተዋል።

ይህም ታዳጊ አገራት በአንድነት ከተነሱና ተባብረው ከሰሩ ከድህነት የመውጣት አቅም እንዳላቸው የሚያሳይ እንደሆነም ተናግረዋል።

"የህዳሴው ግድብ ፍፃሜውን እስኪያገኝ ድረስ ህዝቡ፣ በሀገር ውስጥና ውጭ የሚገኙ ምሁራን ሁሉም ከመንግስት ጎን በመቆም  ድጋፋቸውን  አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባልም" ብለዋል 


 

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለሀገሪቱ እድገት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው የተናገሩት የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የምርምር፣ ማህበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ኤሊያስ አብዱላሂ ፤ይህን ለሁሉም በፍትሃዊነት የሚጠቅም አኩሪ ፕሮጀክት መደገፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ምሁራን ይህን እውነታ ለአለም ለማሳወቅ በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ግድቡ ለሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት የሚጠቅም እንደሆነ በማስገንዘብ ተሳትፏችንን  ማጠናከር አለብን ሲሉ ተናግረዋል።

ይህም  በጥናትና ምርምር አውጥቶ ማሳየት ይገባል ብለዋል።

በተጨማሪም ከፍተኛው የትምህርት ተቋማት ስለ ግድቡ ብቻም ሳይሆን ስለ አባይ ውሃ በስርዓተ ትምህርት ውስጥ አካተው ማስተማር እንዳለባቸውም አስተያየት ሰጥተዋል።


 

 የዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሀብታሙ ተመስገን በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ወንዞችን ወደ ልማት መቀየር ለሁንተናዊ እድገት ወሳኝ ነው ብለዋል።

ለዚህም በተለይ የአባይ ወንዝ ላይ እየተሰራ ያለው የህዳሴው ግድብ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"ከግድቡ ጋር ተያይዞ  ሊደርሱ የሚችሉ ጫናዎችን በማርገቡ ረገድ ከዚህ ቀደም ምሁራንና ዲያስፖራው የሰሩት ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ ትልቅ ውጤት ማምጣቱንና ይህን ስራ አጠናክሮ ከማስቀጠልም ባለፈ  እይታን በማስፋት የቀይ ባህርና ሌሎች ተፋሰሶች ላይ መሠራት ይገባል" ብለዋል።

ምሁራኑ እንዳመለከቱት፤ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ዲፕሎማሲያዊ በሆነ አካሄድ ፍትሃዊ  የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋገጥ መሆኑን ደጋግሞ ማሳየት ያስፈልጋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የህዳሴው ግድብን አራተኛ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የግድቡ በስኬት መቀጠል ሀገራችን በአባይ ወንዝ ላይ የያዘችውን የፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህን ዳር ለማድረስ የሚያስችልና መንግስት የገባውን ቃል በተግባር ያረጋገጠበት ግዙፍ  ፕሮጀክት ነው።

ይህም ሀገሪቱ ኢንዱስትሪዎችንና ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋት እድገትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ  የፈጠረ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም