ቀጥታ፡

በክልሎቹ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን የልህቀትና የስራ ፈጠራ ማዕከል ለማድረግ በግብዓት የማደራጀት ስራዎች እየተከናወኑ ነው

ሐዋሳ/ዲላ/ሆሳዕና፤ ታህሳስ 17/2016 (ኢዜአ) ፡- በክልሎቹ  የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን የልህቀትና የስራ ፈጠራ ማዕከላት ለማድረግ በግብዓት የማደራጀትና የማብቃት ስራ  እያከናወኑ መሆኑን የሲዳማ፣ የደቡብ ኢትዮጵያና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮዎች ገለጹ።  

በተያዘው የትምህርት ዘመን ገበያን መሰረት ያደረጉ የስልጠና ዘርፎችን በጥናት በመለየት ከ50 ሺህ የሚልቁ ሰልጣኞችን ለመቀበል ዝግጅት በማጠናቀቅ ወደ ትግበራ መግባታቸውንም ቢሮዎቹ አመልክተዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዮት ደምሴ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በክልሉ 6 የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆችን ጨምሮ 41 የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ወጣቶችን እያሰለጠኑ ነው።


 

በተያዘው የትምህርት ዘመን የመቁረጫ ነጥቡን ያሟሉ ከ16 ሺህ የሚልቁ ሰልጣኞችን ለመቀበል የሚያስችል ዝግጅት አጠናቀው ወደ ትግበራ መግባታቸውን በማከል።

ተቋማቱ በርካታ ወጣቶችን የሙያ ባለቤት በማድረግ ለክልሉ እድገት መሰረት የሚጥሉ ቢሆኑም ጠቀሜታቸውን በአግባቡ ያለመረዳትና የግብዓት እጥረት ዘርፉን በሚፈለገው መልኩ አላሰኬዱትም" ብለዋል።

ችግሩ ተፈቶ ጥራትን መሰረት ያደረገ ሰልጠናና ትምህርት መስጠት ላይ መተኮሩን ጠቅሰው፤ ፍላጎት መፍጠር ላይም በየደረጃው እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

"ገበያውን መሰረት ያደረገ የስልጠና ዘርፎችን በጥናት በመለየት ወደ ትግበራ መገባቱን ጠቁመው፤ በዚህም ተቋማቱን የስራ እድል ፈጠራና የልህቀት ማዕከላት ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው" ብለዋል።

የግብዓት ውስንነት ያለባቸውን ተቋማት ለይቶ የማደራጀቱ ስራ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ ድጋፎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የሲዳማ ክልል ስራ ክህሎትና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሀገረጽዮን አበበ በበኩላቸው፤ በክልሉ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጆች ብቁና በክህሎት የዳበረ የሰው ሃይል ማፍሪያ እንዲሆኑ በግብአትና በሰው ሃይል የማደራጀት ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

ለዚህም የክልሉ መንግስት ባደረገው ድጋፍ የውስጥ አቅማቸውን ለማጠናከርና ጥራት ያለውን ስልጠና ለመስጠት እንዲያስችላቸው ከ110 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ ማሽነሪዎችን የማሟላትና የማብቃት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን  ነው ያመለከቱት።

በተለይም ወቅቱ የሚፈልገውን ብቁ የሰው ሃይል ከማፍራት አንጻር ያለውን ሚና በአግባቡ እንዲወጡ ከአመለካከት ለውጥ አንስተው የውስጥ አደረጃጀትና የአመራር ብቃት ማስተካከል ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተቋማቱ ወጣቶች ሰልጥነው የሚቀመጡበት ሳይሆን በሙያና ክህሎት በቅተው ከራሳቸው አልፈው ለአከባቢያቸውና ለሀገር እንዲበቁ ገበያን መሰረት ያደረጉ የሙያ ዘርፎች ተለይተው ቅበላ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።

 በዚህ ዓመት የስልጠናን ጥራትና አግባብነት በማጠናከር ባሉት 11 ኮሌጆች ከ14 ሺህ በላይ ሰልጣኞችን በመደበኛነት ተቀብሎ ለማሰልጠን አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ቅበላ መጀመሩን አንስተዋል።

እንደ ሀገር የተጀመረውን ሪፎርም በመከተል ክልላዊ የትኩረት አቅጣጫዎች መለየታቸውን ሃላፊዋ ጨምረው ገልጸዋል።

በዚህም የኮሌጆች የውስጥ አቅምና አመራርን በማጠናከር የበቃና ወቅቱ የሚፈልገውን ክህሎት ያዳበረ የሰው ሃይል ለማፍራት እንዲችሉ አስፈላጊው ሁሉ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ነው ያነሱት።


 

 የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት በሙያ ክህሎት የበቁ ከስራ ጠባቂነት ይልቅ ስራ ፈጣሪ ዜጎችን የማፍራት ሃላፊነቱን ለመወጣት እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ ይርጋ ሃንዲሶ ናቸው።  

በተቋማቱ የስልጠና ጥራትና የደረጃ ማሻሻያ በማድረግ የክልሉ መንግስት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት መስጠቱንም አክለዋል።

በተያዘው ዓመትም በክልሉ በሚገኙ 37 የግልና የመንግስት የትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች ከ20 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስልጠን በቂ ዝግጅት በማድረግ ወደ ትግበራ መግባቱን ገልጸዋል።

ወደ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች መምጣት ማለት ተማሪዎች በሙያቸው ሰርተው ራሳቸውንም አገራቸውንም የሚለዉጡበትን መስክ እንደመረጡ አውቀው መቀጠል እንዲችሉ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም