ቀጥታ፡

በሀገራዊ ምክክሩ አካል ጉዳተኞች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፤ ታህሣስ 17/2016 (ኢዜአ)፡- በሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን አካል ጉዳተኞች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ለማስቻል የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ገለጸ። 

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገሪቱ በሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካና የኃሳብ መሪዎች እንዲሁም በኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች በተመለከተ ያለውን ልዩነት በምክክር ለመፍታት በ2014 ዓ.ም ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል።   

አሁን ላይም ኮሚሽኑ በ700 ወረዳዎች ተሳታፊዎችን የመለየትና የአጀንዳ ኃሳብ የሚሰጡ ተወካዮቻቸውን በመምረጥ ላይ የሚገኝ ሲሆን በትግራይና አማራ ክልል ተሳታፊዎችን ለመለየት ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑን ገልጿል።

በቅርቡም ኮሚሽኑ የአጀንዳ ኃሳቦችን ወደ ማሰባሰብ ምዕራፍ እንደሚሸጋገር ተመላክቷል።  

ሀገራዊ ምክክር የታለመለትን ግብ እንዲያሳካ ኮሚሽኑ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን በተደጋጋሚ የሚገለጽ ሲሆን ይህንን መነሻ በማድረግ ኢዜአ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን አነጋግሯል። 

የፌዴሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጆ፤ በሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት በሚያጋጥሙ የጸጥታ ችግሮች ሳቢያ ዜጎች ለማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ተጋላጭ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

ለዚህም በማያግባቡ አጀንዳዎች ላይ ቁጭ ብሎ ተወያይቶ ዘላቂ መፍትሄ ስላልተበጀ ነው ብለዋል።  

አንድ አገር እንደ አገር እንድትቀጥል ሰላም ወሳኝ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ለዚህም ለግጭትና ሰላም መደፍረስ ምክንያት የሚሆኑ ጉዳዮችን በውይይት እልባት መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት።  

ከዚህ አንጻር ልዩነቶችን በምክክር ለመፍታት የተቋቋመው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሁነኛ መፍትሄ መሆኑ ጠቁመዋል ለምክክሩ ውጤታማነት የሁሉም ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።   

ፌዴሬሽኑም አካል ጉዳተኞች በምክክሩ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ የሚያስችል የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እየተከናወኑ መሆኑን ነው የተናገሩት።  

ኮሚሽኑ በተለያዩ አደረጃጀቶች የሚያከናውናቸው ሥራዎችም አካል ጉዳተኞችን ያካተተ እንዲሆን ከኮሚሽኑ ጋር  የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ምክክሩን ስኬታማ ለማድረግ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አካል ጉዳተኞች የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ለማስቻል ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም