ቀጥታ፡

በምስራቅ ቦረና ዞን ሁለተኛው ዙር የቤት እንስሳት ክትባት እየተሰጠ ነው

ነገሌ ቦረና፤ታህሳስ 17/2016  (ኢዜአ) ፦ በሞቃታማው የምስራቅ ቦረና ዞን አልፎ አልፎ የሚከሰተውን የቤት እንስሳት በሽታን ለመከላከል የሚያስችል ሁለተኛ ዙር የክትባት ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

ምስራቅ ቦረና ሞቃታማና ዝናብ አጠር ዞን እንደመሆኑ የሰብል ልማት በተወሰነ ደረጃ የሚካሄድበትና  የእንስሳት እርባታ በብዛት የሚካሄድበት ዞን ነው፡፡

በዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የእንስሳት ጤና ባለሙያ ዶክተር ገልማ ሊበን እንደሚሉት የእንስሳት ክትባት ሂደት መርሃ ግብሩ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ከታህሳስ 01 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ነው፡፡ 


 

በዞኑ የክረምት ዝናብ መጀመሪያ ወቅትና በበጋ የጸሐይ ሙቀት ሲበረታ አልፎ አልፎ የእንስሳት ጤና ችግር እንደሚያጋጥም ጠቅሰዋል፡፡

ይኸን ድንገተኛ ወረርሽኝ አስቀድሞ ለመከላከል እንዲቻልም ወቅቱን ጠብቆ የቤት እንስሳት የክትባት ዘመቻ  ሲካሄድ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ሁለተኛው ዙር የሆነውን ክትባት ለመስጠት 224 የእንስሳት ሐኪሞችና በርካታ ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞች በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች መሰማራታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ክትባቱ የጎሮርሳ፣ የቆዳና የውሻ በሽታ፣ የሳንባ ምች፣ አባ ጎርባ፣ የአባ ሳንጋና ሌሎች ከሙቀትና ከጸሐይ ብርታት የሚመጡ በሽታዎችን አስቀድሞ ለመከላከል ነው ብለዋል፡፡

የክትባት መርሃ ግብሩ ድመት፣ ውሻና የጋማ ከብቶችን ጨምሮ ለ5 ሚሊዮን 296 ሺህ 842 የቤት እንስሳት እንደሚዳረስ ተናግረዋል፡፡

ክትባቱን ከሚሰጣቸው እንስሳት መካከል ከ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚበልጡት በጎች፣ ፍየሎችና የቀንድ ከብቶች እንደሆኑ በማከል፡፡

በዞኑ 8ቱ ወረዳዎች እስካሁን በተካሄደው የክትባት ዘመቻ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የቤት እንስሳት መከተባቸውን አስታውቀዋል፡፡

ለክትባት መርሃ ግብሩ ከኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ አስፈላጊ የሆነ ፈሳሽና ደረቅ መድሃኒት መቅረቡን ገልጸዋል፡፡ 

በዞኑ በመጀመሪያው ዙር የክትባት መርሃ ግብር 5 ሚሊዮን 139 ለሚሆኑት የቤት እንስሳት በመሰጠቱ በዞኑ የእንስሳት በሽታ አለማጋጠሙን ጠቅሰዋል፡፡

ያላቸውን እንስሳት እያስከተቡ ከሚገኙ የዞኑ አርሶ አደሮች መካከል የዳስ ወረዳ ነዋሪ አቶ መስፍን መኩሪያ እንዳሉት ቋሚ መተዳደሪያቸው ከእንስሳት እርባታ ከሚያገኙት ምርት ነው፡፡

በተያዘው በጋ ሊከሰት ከሚችል በሽታ ለመከላከል እስከ ቤት ድረስ በመጡ የእንስሳት ሐኪሞች ሁሉንም ከብቶቻቸውን በማስከተባቸው ለባለሙያዎቹ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አቶ ቦራ ሀላኬ በበኩላቸው ከዋና ከተማ የራቀ ስፍራ ስለሚኖሩ የቤት እንስሳቶቻቸውን ለማሳከም እንደሚከብዳቸው ይገልጻሉ፡፡

በጸሐይና ከውሃ ጥም የሚነሳ ከውሻ ወደ እንስሳ ከዚያም ወደ ሰው የሚተላለፍ የቆዳና የውሻ በሽታ በጋ ሲመጣ የእለት ከእለት ስጋት እንደሚሆንባቸው ገልጸው፤ "ችግራችንን የተረዳው መንግስት ሐኪሞችን ቤት ድረስ ልኮልን ከስጋት ነጻ አድርጎናል" ብለዋል፡፡

''ክትባቱ ከብቶቻችንን ከተለያዩ በሽታዎች የሚያድንልን በመሆኑ የነበረንን ስጋት አስቀርቶልናል'' ብለዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም