ቀጥታ፡

የባህር በር የማግኘት ጥያቄው እንዲሳካ ጠንካራ የውስጥና የውጭ ዲፕሎማሲ ሥራ መስራት ያስፈልጋል-የዩኒቨርሲቲ ምሁራን

አርባ ምንጭ፤ ታህሳስ 17/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ እንዲሳካ ጠንካራ የውስጥና የውጭ ዲፕሎማሲ ሥራ መስራት እንደሚገባ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከል አስተባባሪና የጋዜጠኝነት መምህር ተስፋዬ አለማየሁ ለኢዜአ እንደገለጹት የኢትዮጵያን ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ ወሳኝና አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።

ኢትዮጵያውያን በባህር በር ላይ አንድ አይነት አመለካከት ሊኖራቸው እንደሚገባ የገለጹት መምህር ተስፋዬ፣ ፍትሃዊና ህጋዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ሁላችንም የሀገራችን ዲፕሎማት መሆን አለበን ብለዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ እንዲሳካም ጠንካራ የውስጥና የውጭ ዲፕሎማሲ ሥራ መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።  

ወደብ ያላቸው ሀገራት ሸቀጦችን በርካሽ ዋጋ ወደ ሀገራቸው የማስገባት ዕድል እንዳላቸው ጠቅሰው፣  የኢትዮጵያን የባህር በር ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማፋጠንና ዜጎችን በዘላቂነት ተጠቃሚ ለማድረግ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ዜጎች በባህር በር ጉዳይ የጋራ አቋም በመያዝ ለሀገራቸው ዲፕሎማት መሆን እንዳለባቸው ነው ያስገነዘቡት።  

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳ አካል ሆኖ መቅረብ እንዳለበትም መምህር ተስፋዬ ጠቁመዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው፣ ሀገራዊና ገዥ ትርክቶችን ከመፍጠር አኳያ በአሁኑ ወቅት መንግስት እያከናወነ ያለው ተግባር ተገቢና ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

የባህር በር ጉዳይን የጋራ ትርክት ከማድረግ ባለፈ ሁሉም ዜጋ በጉዳዩ ላይ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የበኩሉን እንዲወጣ ጉዳዩን በሚገባ ማስረጽ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የራሷን የባህር በር ለማግኘት የጀመረቻቸውን እንቅስቃሴዎች በሰላማዊ፣ በዲፕሎማሲያዊና በህጋዊ መንገድ ማስቀጠል እንደሚገባ ያመለከቱት ዶክተር ዳምጠው፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ሳይንሳዊ፣ ታሪካዊ እና ህጋዊ ምክንያቶችን በማቅረብ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የባህር በር እና አማራጭ የወደብ ጥያቄ የፖለቲካ ጉዳይ ሳይሆን የህዝቡ የህልውና ጉዳይ ነው ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ቢዝነስ ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ታሪኳ ወልደመድህን ናቸው፡፡

የውጭና የውስጥ የዲፕሎማሲ ስራን በማጠናከር ኢትዮጵያ ያነሳችው የባህር በር ጥያቄ ተገቢ ምላሽ እንዲያገኝ ዜጎች በያሉበት አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸውም አመልክተዋል። 

በዓለም የባህር በር ከሌላቸው ሀገራት በህዝብ ብዛት ኢትዮጵያ ቀዳሚ መሆኗን ጠቁመው፣ ይህም በፖለቲካም ይሁን በምጣኔ ሀብት ረገድ ሊፈጠር የሚችለው ሀገራዊና ቀጣናዊ ጫና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል። 

በመሆኑም መንግስት ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ መሰረት ያደረገ የማግባባት ሥራ መስራት እንዳለበትም አመልክተዋል።

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ “የባህር በር የልማት በር” በሚል መሪ ቃል ከዩኒቨርሲቲው ምሁራንና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ሰሞኑን ውይይት ማካሄዱ የሚታወስ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም