የክልሉ ሁለንተናዊ የልማትና የሰላም ጥረቶች እንዲሳኩ የተቀናጀ ጥረት ይደረጋል - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉ ሁለንተናዊ የልማትና የሰላም ጥረቶች እንዲሳኩ የተቀናጀ ጥረት ይደረጋል
ሆሳዕና፤ ታህሳስ 16 /2016 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እየተከናወኑ የሚገኙ ሁለንተናዊ የልማትና የሰላም ተግባራት ከግብ እንዲደርሱ በተቀናጀ መልኩ በመንቀሳቀስ የሚጠበቅበትን እንደሚወጣ የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ ።
ምክር ቤቱ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ የሚጠበቅበትን እንደሚወጣም ገልጿል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት 14 ክልላዊና ሀገራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማቀፍ በዛሬው ዕለት ተመስርቷል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው የተመረጡት ወይዘሮ ነይማ ሙኒር ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የክልሉን ሁለንተናዊ ልማትና ሰላምን የማረጋገጥ ጥረቶች ከግብ እንዲደርሱ ምክር ቤቱ የሚጠበቅበትን ይወጣል ።
ለዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቀራርበውና ተቀናጅተው እንደሚሰሩ ገልጸው በተለይም የጋራ የሆኑ እሳቤዎችን በማስጠበቅ ለልማትና ለሰላም በጋራ እንደሚቆሙ ተናግረዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በተከታዮቻቸው ዘንድ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በማጠናከር ዘላቂ ሰላም እንዲጎለብት ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በተለይም ከነጠላ ትርክትና ላለመግባባት ምክንያት ከሚሆኑ ዕሳቤዎች በመላቀቅ የጋራና የወል ዕሳቤዎችን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ ተናግረዋል።
የክልሉን ህዝብ በማቀራረብ የሚፈልገውን ለውጥ ለማምጣትና ለዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ እንደሚሰሩ የተናገሩት ደግሞ በጋራ ምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ አጫሞ ቦቄ ናቸው።
ከዚህ ቀደም ለፖለቲካ ትርፍ መጠበቅና ለግል ተጠቃሚነት መረጋገጥ በተሰሩ ስራዎች በህዝቡ መካከል የልዩነት እሴት እንዲዳብር ያደረጉ አመለካከቶች እንዲወገዱ ይሰራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ዶክተር መብራቱ ዓለሙ በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ከሚያራርቁን ይልቅ በሚያቀራርቡን ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይገባናል ብለዋል።
የክልሉን ልማትና ሰላም ለማጠናከር አደረጃጀቱ ጠቃሚ መሆኑን አንስተው በተቀናጀ መንገድ የልማትና የሰላም እንዲሁም የህዝብ ፍላጎቶች እንዲመለሱ መትጋት ይጠበቃል ነው ያሉት።
የጋራ ምክር ቤቱ የተቋቋመበት ዓላማም ይህ ነው ያሉት ዶክተር መብራቱ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲመዘገብ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዙ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምስረታ ጉባኤ ላይ 14 የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ተሳትፈዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ በመስራች ጉባኤው አምስት የስራ አስፈፃሚ አባላትን የመረጠ ሲሆን ቃለ መሃላ በማስፈፀም መድረኩን አጠናቋል።