ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙኃን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራዎች ሰፊ ሽፋን በመስጠት ዜጎችን ማስገንዘብ ይጠበቅባቸዋል - አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ 

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 16/2016 (ኢዜአ)፦ መገናኛ ብዙኃን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራዎች ሰፊ ሽፋን በመስጠት ዜጎች ፋይዳውን እንዲገነዘቡ የማድረግ ኃላፊነት እንደሚጠበቅባቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ አሳሰቡ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሥራ አፈፃጸምንና ሱፐርቪዥን ሪፖርትን አስመልክቶ ውይይት አካሂዷል። 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፤ ኢትዮጵያውያን በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ መግባባትን በመፍጠር ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች አገር ለማስረከብ ምክክር ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

መንግስት ለዜጎች በገባው ቃል መሰረት ለሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ስኬት በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ የሚያደርገውን እገዛ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ህብረተሰቡ ለኮሚሽኑ እያደረገው ያለው እገዛ ልዩነትን በምክክር ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው የሚያሳይ መሆኑን አፈ-ጉባኤው ጠቅሰዋል፡፡


 

በቀጣይም ኮሚሽኑ ገለልተኝነትን በጠበቀ መልኩ የጀመረውን ሂደት በስኬት እንዲቋጭ ድጋፉን የማስቀጠል ታሪካዊ ኃላፊነት አለብን ብለዋል።

ብሔራዊ መግባባት የተፈጠረባትና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትወልድ ለማስረከብ ለህዝቡ የተገባውን ቃል ለማሳካትም መንግስት ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አንስተዋል።

መገናኛ ብዙኃን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራዎች ሰፊ ሽፋን በመስጠት ዜጎችን የማስገንዘብ ስራዎችን አጠናክረው መቀጠል እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል። 

የምክር ቤቱ ተጠሪ ተቋማት እና ባለድርሻ አካላትም የጋራ አጀንዳ ለሆነው የምክክር ሂደት መሳካት ርብርብ ማድረግ እንደሚኖርባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።


 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ፤ ኮሚሽኑ በተሳታፊና አጀንዳ ልየታ ሁሉንም ማህበረሰብ ያሳተፈ ለማድረግ እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል።

የምክክር ሂደቱን በጥራት ለመምራት የሚዲያ እና ተግባቦት ሥራውን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፥ በመስክ ምልከታ መነሻነት የቀረቡ አስተያየቶችን በመውሰድ የተጣለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት እንሰራለን ብለዋል። 

ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬትም ከኃይማኖት ተቋማት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከመምህራን፣ ከወረዳ ዳኞችና አስተዳደሮች፣ ከዕድሮችና ሲቪክ ማህበራት ጋር በቅርበት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በሂደቱም መገናኛ ብዙሃን የምክክር ኮሚሽኑን ዓላማና እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን ለማህበረሰቡ የማሳወቅና የማስገንዘብ ስራቸውን አጠናክረው እንዲያስቀጥሉ ጠይቀዋል። 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ ኮሚሽኑ እያከናወነ የሚገኘውን ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል። 

የኮሚሽኑን ተግባራት ማህበረሰቡ እንዲገነዘብ ለማስቻል የኮሙዩኒኬሽንና ተግባቦት ስራዎችን ቀጣይነት ባለው መልኩ መምራት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

በውይይቱ የተሳተፉት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎትና የመገናኛ ብዙኃን የሥራ ኃላፊዎች የምክክር ኮሚሽኑን ዓላማ እውን ለማድረግ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል። 


 

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ፤ ዜጎች ለምክክር ሂደቱ ስኬት በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል ከሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ተቋማት ጋር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ፤ ብሔራዊ መግባባትን እንዲፈጠር መስራት የኢዜአ ግንባር ቀደም ተልዕኮ በመሆኑ ከኮሚሽኑ ጋር በቅርበት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል። 


 

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ታደሰ፤ የሀገራዊ ምክክር ስራዎችን ህብረተሰቡ እንዲገነዘብ ለማስቻል እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።


 

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለዜጎች ብሔራዊ መግባባት ያለውን ወሳኝነት የማሳወቅ ስራ እንሰራለን ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መሳፍንት ተፈራ ናቸው።


 

ቋሚ ኮሚቴው በሲዳማ፣ ሀረሪ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች እና በኮሚሽኑ ዋና መስሪያ ቤት በመገኘት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን የስራ እንቅስቃሴን እንደተመለከተ በሪፖርት ቀርቧል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም